የአውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዝዳንት በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ጉዳይ ከኬንያ ጋር ተወያዩ
ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ትናንት ለአንድ ቀን ጉብኝት ወደ ናይሮቢ አቅንተው እንደነበር ይታወሳል
ቦሬል ኬንያ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ያላትን “ቁልፍ ሚና” ገልጸዋል
በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ ከኬንያ የመከላከያ ሚኒስትር ሞኒካ ጁማ ጋር ረጅም ውይይት ማድረጋቸውን የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ እና ደህንነት ፖሊሲ ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦሬል አስታወቁ፡፡
ቦሬል ኬንያ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ያላትን “ቁልፍ ሚና” ገልጸዋል፡፡
ትናንት ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ጋር ስልክ ተደዋውለው እንደነበር የገለጹት ቦሬል “ታሪካዊ” ሲሉ የተናገሩለት የሱዳን ሽግግር በምንም ዓይነት መልኩ “በቀጣናዊ ችግሮች ምክንያት እንዲደናቀፍ አንፈቅድም” ሲሉ በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው መጻፋቸውን አል ዐይን አማርኛ መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡
የኬንያን የምስራቅ አፍሪካ ኃያልነት እና ወሳኝነት ሲገልጹ ቦሬል የመጀመሪያው አይደሉም፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያ ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ይህንኑ ነገር ስለማለታቸው ተዘግቧል፡፡
ይህ ምናልባትም ምዕራባውያኑ ከአሁን ቀደም የምስራቅ አፍሪካ ቁልፍ አጋር አድርገው ይመለከቷት ለነበረችው ኢትዮጵያ ያላቸው የግንኙነት አተያይ መቀየሩን ሊያመለክት እንደሚችል ይገመታል፡፡
ኬንያ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ናት፡፡ ለቀጣዮቹ 2 ዓመታትም በዚሁ ሚናዋ ትቀጥላለች፡፡ የአፍሪካ ህብረት የጸጥታው ምክር ቤት አባል መሆኗም ይታወቃል፡፡
ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ትናንት ለአንድ ቀን ጉብኝት ወደ ናይሮቢ አቅንተው እንደነበርም አይዘነጋም፡፡