እንቁላልን የመመገብ ጤና በረከቶች ምን ምን ናቸው?
በቀን አንድ እንቁላል የሚመገቡ ሰዎች የልብ ህመምን ጨምሮ ከበርካታ በሽታዎች የመጠበቅ እድላቸው ከፍተኛ ነው ተብሏል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/10/258-131439-whatsapp-image-2025-02-10-at-12.14.25-pm_700x400.jpeg)
እንቁላል በፕሮቲን ይዘቱ የበለጸገ መሆኑ በርካታ ቫይታሚኖችን ያስገኛል
እንቁላልን የመመገብ ጤና በረከቶች ምን ምን ናቸው?
የአውስትራሊያው ሞናሽ ዩንቨርሲቲ 70 ዓመት እና ከዛ በላይ እድሜ ባላቸው ሰዎች ከእንቁላል አመጋገብ ጋር በተያያዘ ያጠናውን ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡
ከ8 ሺህ በላይ ሰዎች በተሳተፉበት በዚህ ጥናት መሰረት በየዕለቱ አንድ እንቁላል የሚመገቡ ሰዎች በወር ሁለት ጊዜ የሚመገቡ ሰዎች የተሻለ ጤነኛ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
በሳምንት ከአንድ እስከ ስድስት እንቁላል የሚመገቡ ሰዎች ከማይመገቡት ጋር ሲነጻጸሩ የመሞት እድላቸው በ15 በመቶ ቀንሷልም ተብሏል፡፡
እንዲሁም በቀንድ አንድ አልያም በሳምንት ስድስት እንቁላል የሚመገቡ ሰዎች ላይ በልብ ህመም ምክንያት የሚመጣ ሞት በ29 በመቶ እንደቀነሰም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
በዩንቨርሲቲው የበሽታ መከላከል መምህር የሆኑት ሆሊ ዊልድ ስለ ጥናቱ ከዩሮ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ላይ እንዳሉት እንቁላል በአዋቂ ሰዎች ላይ ያለው የጤና ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንቁላል በፕሮቲን ይዘቱ የበለጸገ ከመሆኑ ባለፈ ለሰው ልጆች ጤና አስፈላጊ የሚባሉት እንደ ቫይታሚን ቢ፣ ፋቲ አሲድ እና ሌሎች ጠቃሚ ማዕድናትን የያዘ ነው፡፡
ከዚህ በፊት እንቁላል ባለው ፕሮቲን ብዛት ምክንያት ለኮሊስትሮል መከማቸት ምክንያት ይሆናል የሚባል ቢሆንም የተመጠነ እንቁላል መመገብ በልብ ህመም የመያዝ እድላችንን የሚቀንስ እንጂ የሚጨምር አለመሆኑ በጥናቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡
በቀን አንድ ወይም በሳምንት ስድስት እንቁላል መመገብ በቂ ነው የተባለ ሲሆን ይህ ከሆነ በሰውነታችን የኮሊስትሮን መጥን እንዳይከማች ያደርጋልም ተብሏል፡፡
የአሜሪካ በሽታ መከላከል እና ቁጥጥር ባለ ስልጣን በ2020 ባወጣው ጥናት መሰረት አንድ ሰው በሳምንት እስከ ሰባት እንቁላል ቢመገብ የጎንዮሽ ጉዳት እንደማያስከትል አስታውቋል፡፡