ለ40 ቀናት ያለ ምግብ እና ውሀ በጫካ ውስጥ ታስራ የሰነበተችው አሜሪካዊት በህይወት መትረፍ አነጋጋሪ ሆኗል
በህንዳዊ ባለቤቷ ካዛፍ ጋር በሰንሰለት ታስራ ለ40 ቀናት የቆየችውን አሜሪካዊት የአካባቢው እረኞች ህይወቷን ታድገዋል
በምግብ እጥረት መናገር እና መንቀሳቀስ የማትችለው ግለሰቧ በስፍራው እንዴት እንደተገኝች በጽሁፍ ለፖሊስ ቃሏን ሰጥታለች
ለ40 ቀናት ያለ ምግብ እና ውሀ በጫካ ውስጥ ታስራ የሰነበተችው አሜሪካዊት በህይወት መትረፍ አነጋጋሪ ሆኗል
ላሊታ ካይ የተባለቸው የ50 አመት አሜሪካዊት ለ40 ቀናት ከዛፍ ጋር በታሰረችበት ጫካ ውስጥ በህይወት መትረፍ ችላለች፡፡
በምዕራባዊ ህንድ ማሻርታ ክልል በሚገኝ ጫካ ውስጥ የድረሱልኝ ጩሀት ስታሰማ በአካባቢው በነበሩ እረኞች የተገኘችው አሜሪካዊት ምግብ እና ውሀ በማታገኝበት ሁኔታ በጫካ ውስጥ ለ40 ቀናት ከዛፍ ጋር በሰንሰለት ታስራ ተገኝታለች፡፡
ጩሀቷን ሰምተው ወደ ስፍራው ያቀኑት እረኞች ወደ ፖሊስ በመደወል በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል እንድትወሰድ አድርገዋል፡፡
በምግብ እና ውሀ እጦት መናገርም ሆነ መንቀሳቀስ በማትችልበት ሁኔታ በጫካ ውስጥ የተገኝችው ግለሰቧ፤ ወደ ሆስፒታል ከተወሰደች በኋላ በሰውነቷ ላይ መሻሻል የታየ ሲሆን የአዕምሮ ጤና ደህንነቷን ለማረጋገጥ ወደ አእምሮ ሆስፒታል መዘዋወሯ ተሰምቷል፡፡
በምግብ እና ውሀ እጥረት በጉሮሮዋ ላይ በደረሰባት ጉዳት በቅጡ መናገር የማትችለው ላሊታ በጽሁፍ ለፖሊስ በሰጠችው ቃል ህንዳዊ በሏ በጫካ ውስጥ ለሞት ጥሏት እንደሄደ ተናግራለች፡፡
ፖሊስ የባለቤቷን ማንነት ካወቀ በኋላ በአቅራቢያው በሚገኙ ከተሞች ተጠርጣሪውን በማፈላለግ ላይ እንደሚገኝ ገልጾ፤ ድርጊቱን ፈጸመ የተባለው የተጎጂዋ ባለቤት ወንጀሉን ለመፈጸም ምን እንዳነሳሳው ተጨማሪ ማጣሪያዎችን እያደረገ እንደሚገኝ አሳውቋል፡፡
ሆኖም ላሊታ ለ40 ቀናት መቆየቷን ከተናገረችው ውጭ ፖሊስ ለምን ያህል ጊዜ በጫካ ውስጥ እንደቆየች ማረጋገጥ አልቻለም፡፡
ግለሰቧን በጫካ ውስጥ ያገኛት የአካባቢው ነዋሪ ፓንዱራንግ ጋውካር ለቢቢሲ እንደተናገረው “በጫካ ውስጥ ከብቶችን እያሰማራሁ ባለሁበት ለቅሶ እና ጩሀት የተቀላቀለበት ድምጽ ሰምቼ ወደ አካባቢው ስጥጋ ሰውነቷ በምግብ እጥረት በእጅጉ የተጎዳች ሴት ከዛፍ ጋር በሰንሰለት ታስራ አገኝሁ፤ ለፖሊስ በሰጠችው ቃል መሰረት ለ40 ቀናት መቆየቷን ስስማ ይህን ያህል ጊዜ ያለ ምግብ እና ውሀ መቆየቷ አስደንቆኛል” ብሏል፡፡
ፖሊስ በአካባቢው ባደረገው ፍተሸ ግለሰቧ የአሜሪካ ዜጋ መሆኗን የሚገልጽ የፓስፖርት ኮፒ እና በህንድ መንግስት የተሰጣት የመኖርያ ፈቃድ ወረቅት አግኝቷል፡፡
በተጨማሪም ግለሰቧ ከ10 አመታት በፊት ዮጋ እና ሜዲቴሽን ለመማር ወደ ህንድ መምጣቷን አረጋግጧል፡፡
በጤናዋ ሁኔታ ላይ ምርመራ ያደረጉት ዶክተሮች ይህን ያህል ቀን ያለ ምግብ የቆየችበት መንገድ አስገራሚ መሆኑን ተናግረው፤ ምናልበታም በአቅራቢያዋ የሚገኙ ቅጠላቅጠሎችን እና ነፍሳትን በመመገብ ህይወቷን ለማቆየት እንደቻለች ጥርጣሬ እንዳለቸው ነው የገለጹት፡፡
እንደዛም ሆኖ ሰውነቷ በምግብ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እንደተጎዳ እና ካሳለፈችው ጭንቀት አንጻር የአዕምሮ ጤናዋም ሳይታወክ እንደማይቀር ለአካባቢው ጋዜጦች ተናግረዋል፡፡