ስጋ እና የተቀነባበሩ ምግቦችን አብዝቶ መመገብ ለመርሳት በሽታ ያጋልጣል ተባለ
አዘውትረው ስጋ የሚመገቡ ሰዎች የአዕምሮ መዛባት አጋጥሟቸዋል ተብሏል
የመርሳት በሽታ የእድሜ ልክ በሽታ ሲሆን ፈዋሽ መድሃኒትም የለውም
ስጋ እና የተቀነባበሩ ምግቦችን አብዝቶ መመገብ ለመርሳት በሽታ ያጋልጣል ተባለ፡፡
የአውስትራሊያ ቦንድ ዩንቨርሲቲ ተመራማሪዎች ይፋ ባደረጉት ጥናት መሰረት ስጋ እና የተቀነባበሩ ምግቦችን አብዝቶ መመገብ ለመርሳት በሽታ ይዳርጋል ተብሏል፡፡
እነዚህ ተመራማሪዎች ለዓመታት ሲያካሂዱት የነበረውን ጥናት ይፋ ያደረጉ ሲሆን ሰዎች ስጋ እና የተቀነባበሩ ምግቦችን አዘውትረው እንዳይመገቡ አሳስበዋል ሲል ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በጥናቱ ላይ 438 ሰዎች ተሳትፈዋል የተባለ ሲሆን ከነዚህ ሰዎች መካከል 108ቱ ሰዎች የመርሳት በሽታ ያለባቸው ሲሆን ቀሪዎቹ 330 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው ነጻ ነበሩ ተብሏል፡፡
ይሁንና ከነዚህ ሰዎች መካከል አዘውትረው ስጋ እና እንደ በርገር፣ ፒዛ፣ ሶስ እና ሌሎች የተቀነባበሩ ምግቦችን ይመገቡ የነበሩት ሰዎች በሽታው ተገኝቶባቸዋል፡፡
ቀይ ስጋ አብዝቶ መመገብ ለስኳር ህመም እንደሚዳርግ ተመራማሪዎች ገለጹ
የጥናቱ ዋና መሪ የሆነችው ታህራ አህመድ እንዳለችው የመርሳት በሽታ በእድሜ ብቻ እንደሚመጣ ቢታመንም አመጋገባችን በአዕምሯችን የማስታወስ አቅም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው አረጋግጠናል ብላለች፡፡
በመሆኑም ሰዎች ስጋ እና የተቀነባበሩ ምግቦችን አዘውትረው እንዳይመገቡ የሳሰቡት ተመራማሪዎቹ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረግ ጎን ለጎን አትክልት እና ፍራፍሬዎችን እንዲመገቡም አሳስበዋል፡፡
የመርሳት በሽታ እስካሁን ፈዋሽ መድሃኒት ያልተገኘለት ሲሆን ገዳይ የሆነ የአዕምሮ በሽታም ነው፡፡
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ በዓለማችን 25 ሚሊዮን ዜጎች በመርሳት በሽታ የተጠቁ ሲሆን 9 ሚሊዮን ገደማ ተጠቂዎች ያሉባት አውሮፓ ከፍተኛ የመርሳት በሽታ ተጠቂዎች ያሉበት አህጉር ነች፡፡