እገዳው የተጣለው ኢቦላ በተሰራጨባቸው ሁለት ግዛቶች ላይ ነው
ኡጋንዳ ኢቦላን ለመከላከል የሰዓት እላፊ መጣሏ ተገለፀ።
ምስራቅ አፍሪካዋ ኡጋንዳ በገዳዩ የኢቦላ ቫይረስ ዳግም በመከሰቱ ከ19 በላይ ዜጎቿን አጥታለች።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልም የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ይህ ገዳይ ቫይረስ የበለጠ በተስፋፋባቸው ሙቤንዴ እና ካሳንዳ በተባሉ ሁለት ግዛቶች ላይ የሰዓት እላፊ መጣሉን ገልጸዋል።
እገዳው ከተጣለባቸው ተግባራት መካከልም በሁለቱ ግዛቶች የአምልኮ ስፍራዎች፣ መዝናኛ ቤቶች እንዲዘጉ ተውስኗል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ለ21 ቀናት ይቆያል የተባለው ይህ እገዳ የህዝብ በአንድ ስፍራ መሰብሰብን ከማገዱ በተጨማሪ የእንቅስቃሴ ገደብም ተጥሏል ተብሏል።
ኡጋንዳ ከአንድ ሳምንት በፊት በመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች የባህላዊ ህክምና እንዳይካሄድ እገዳ መጣሉ ይታወሳል።
በኢቦላ ቫይረስ ተጠቅተው ህይወታቸው ካለፉ ኡጋንዳዊያን ውስጥ የህክምና ባለሙያዎቿን በዚሁ ቫይረስ ማጣቷ ተገልጿል።
የኢቦላ ቫይረስ ከዚህ በፊት በምዕራብ አፍሪካ ባሉ ሀገራት ላይ ማለትም ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ተከስቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን መግደሉ አይዘነጋም።