በኢቦላ ላይ የዘመተው የኢትዮጵያ የጤና ቡድን በኮሮና ላይስ እየዘመተ ይሆን?
በምእራብ አፍሪካ በኢቦላው ላይ የዘመተው የኢትዮጵያ የጤና ቡድን ኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር በምን መልኩ እያገዘ ነው?
“አሁን ባለው እንዝህላልነትና መዘናጋት ከቀጠልን ግን እነ ጣሊያን ሌሎችም እያጋጠማቸው ያለው ችግር ላለማጋጠሙ ምንም ዋስትና የለንም”-አቶ ህንፃ
“አሁን ባለው እንዝህላልነትና መዘናጋት ከቀጠልን ግን እነ ጣሊያን ሌሎችም እያጋጠማቸው ያለው ችግር ላለማጋጠሙ ምንም ዋስትና የለንም”-አቶ ህንፃ
በ2007 ዓ.ም በምእራብ አፍሪካ ኢቦላ ተከስቶ በነበረት ጊዜ ከኢትዮጵያ 186 የሚሆኑ በጎፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎችን የመሩትንና የኢቦላን አስከፊ ገጽታ ያዩት አቶ ህንፃ ሀዱሽ ከአል-አይን አማርኛ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡አቶ ህንፃን ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ስለተከሰተውና አለምአቀፋዊ ስለሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጠይቀናቸዋል፡፡ የኢቦላ ቫይረስ ከኮሮና ቫይረስ/ኮቪድ 19 በምን ይለያል? ኢቦላን በመከላከል የተገኘውን ልምድስ በምን መልኩ ለመንግስት አካፈሉት፤ኮሮና ቫይረስን ለመከላከልስ ምን መደረግ አለበት?ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ሰጥተውናል፡፡ አዲስ አበባ በኛ ኮንቴክስት/ሀገር የቫይረሱ ማእከል ነች፡፡ ኬዝ የሚበዛ ከሆነ አዲስ አባባን ሎክ[መዝጋት] እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ አቶ ሀዱሽ አሁን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፍትሀዊነትና ጤና ስርአት ማጠናከር ባለሙያ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
ከአቶ ህንፃ ጋር ያደረግነውን ሙሉ ቃለ-ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
አል-ዐይን፡ በ2007 ዓ.ም (እ.ኤ.አ በ2014) በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተውን ወረርሽኝ ተከትሎ ኢትዮጵያ ወደ ሥፍራው የጤና ቡድን ልካ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን የሰራው ምን ነበር?
አቶ ህንፃ፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያቀረቡትን የዕርዳታ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት 210 ባለሙያዎች ለመላክ ፈቃደኛ ሆና ከ210 ውስጥ 186 ባለሙያዎች እዛው ተሰማርተን ሄደናል፡፡ እንግዲህ በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ሁላችንም የምናስታውሰው ነው፡፡ ዓለምን ያስጨነቀ ነበር፡፡ ሁሉም የፕሪንትና ኦዲዮ ቪዠዋል ሚዲያዎችን በጣም አስጨናቂ ምስሎችን ያሰራጩበት ነበረ፡፡ በወቅቱ ወደዛ መሄድ ከፍተኛ ፍርሃትና ጭንቀት የሚፈጥር ነው፡፡ ነገር ግን የኛ ቲም በጊዜው በቂ ሥልጠና ወስደን ነው የሄድነው፤ እዛም በቂ ሥልጠና ወስደን ነው የገባነው፡፡ ይህ በዋናነት ኢቦላና ኬዝ ማከም ሰርቪላንስ እንዲሁም መከላከል ላይ ነው ያተኮረ ስልጠናን ወስደን ስለመሄዳችን ማሳያ ነው፡፡
አል-ዐይን: በተግባር እዛ ሄዳችሁ ምን ሰራችሁ?
አቶ ህንፃ፡ መጀመሪያ ቅኝት ነው ያካሄድነው ምንድን ነው እዛ ቦታ ላይ ያለው አሁን ለምሳሌ፤ ላይቤሪያ እኛ በደረስንበት ወቅት ሁሉም የሃገሪቱ የጤና እና የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት በሙሉ ዝግ ነበሩ፡፡ ከተወሰኑ ሱፐርማርኬቶች ውጭ እንቅስቃሴም የለም፡፡ በሙሉ ሲስተሙ ዲስትሮይድ/ተበላሽቶ ነው ያገኘነው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ በዚህ ሁኔታ ምን ልንሰራ እንደምንችል የሚያሳይ ጥናት ነው ያካሄድነው፡፡ በጥናቱ መሰረትም ወደ ትግበራ ገባን፡፡ የአፍሪካ ህብረት እና የናይጀሪያ የበጎ ፍቃድ ቡድን አባላትም ገብተው ነበር የቆዩን፡፡ 182 አባላት ያሉት የናይጀሪያ ቲም አንድ ሳምንት ቀድሞ በስፍራው ቢደርስም ባደረባቸው ፍራቻ በማረፊያቸው ተቀምጠው ነበር የቆዩን፡፡ ስለዚህ በጥናቱ መሰረት እዛው ሥልጠና ሰጠን፡፡ ከዓለም ጤና ድርጅት፣ ከአሜሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል እና ከአፍሪካ ህብረት እንዲሁም የሃገሪቱ የጤናና መከላከያ ሚኒስቴሮች ካቋቋሙት ምላሽ ሰጪ ቡድን ጋር ሆነንም እንደየዘርፋችን ተግባራዊ ስልጠና ተሰጠን፡፡ ስልጠናው እንደተጠናቀቀም ወደየ ሳይቱ አሰራጨን፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር ቆሞ ስለነበር ስራው አልጋባልጋ አልሆነልንም፡፡
አል-ዐይን፡ የአፍሪካ የጤና ሁኔታ ደካማ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የላይቤሪያ፣የሴራሊዮንና የጊኒ የጤና ስርዓት ምን ይመስል ነበር?
አቶ ህንፃ፡ አዎ በጊዜው አብዛኞቹ የመንግስት ኃላፊዎች ሸሽተው ነበረ፡፡ ፈርተው ሸሽተው ወደ ምዕራባውያን አብዛኞቹ ወደ አሜሪካ፣ የሴራሊዮን ወደ እንግሊዝ የጊኒ ደግሞ ወደ ፈረንሳይ ሸሽተውም ነበር፡፡ የነበረው የጤና ስርዓትም ፈርሶ ነበር ያገኘነው፡፡ እውነት ለመናገር የሃገራቱ የጤና ሥርዓት እዚህ ደካማ ከምንላቸው ዞኖች ወይም ክልሎች በታች ነበር፡፡ አደረጃጀቱ ፣የሰው ሃይል ስምሪቱ፣ የሎጀስቲክ አቅርቦቱ አጠቃላይ የመረጃ ልውውጡ ደካማ ነበር፡፡ የባለሙያው የመስራት ፍላጎት ተነሳሽነት በሽታን የመከላከል እኛ ከ10 ዓመት በፊት የተውናቸውን ህክምና አሰጣጥ ስታንዳርዶች ሲተገብሩ ነው እዛ ያገኘናቸው፡፡
አል-ዐይን፡ የዓለም ጤና ድርጅት ኢቦላን ወረርሽኝ ነው ብሎት ነበር፡፡ እዚያ በነበራችሁበት ጊዜ መቆጣጠር ይቻላል የሚል ነገር ነበር፤ እንዴትስ መቆጣጠር ተቻለ?
አቶ ህንፃ፡ አንድ የሀገራቱ መንግስታት ተጠናከሩ፣ ህብረቱ ከመከላከያ፣ከፖሊስ፣ ከሲቪል የተውጣጡ 855 ባለሙያዎችን አሰማራ፡፡ የሁሉም ሃገራት ባለሙያዎች ተመድበው የበሽታ ቅኝቱ ተጠናከረ፤ በየቀኑ የሚመጡ ዳታዎችን ሰብስቦ የሚተነትን አይ.ኤም.ኤስ የሚባል (incident management system ) አቋቋምን ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢቦላ ኬዝ ከተገኘ የተገኘበት ቦታ ሄዶ ለይቶ የሚቆይና የሚጠብቅ ሙቀት መቆጣጠሪያና ሌሎች ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች እንዳይኖሩ እዛው ሆኖ የሚቆጣጠር ቲም በማቋቋም አጠቃላይ የጤና ስርዓቱን ነው ከላይ እስከ ታች በደንብ ያገዝነው፡፡ህመምተኞቹ ተኝተውባቸው የነበሩና በተረጨው ኬሚካል ሻግተው የፈረሱ የተዘጉ የጤና ተቋማት ታድሰው ተከፈቱ ፤ የራሳችንን ባለሙያዎች መድበን እንደገና አሰማርተን ነው ስርዓቱን አሻሻልው፡፡
አል-ዐይን፡ አሁን ላይ ከኢቦላ በበለጠ የሰው ልጆችን ስጋት ውስጥ የከተተ ኮሮና ቫይረሰ/ ኮቪድ 19 የሚባል ወረርሽኝ ተከስቷል፡፡ በኢቦላ የነበራችሁ ልምድ ኮቪድ 19 ለመከላከል በምን መልኩ ይጠቅማል?
አቶ ህንፃ፡ ኖቭል ኮሮና ቫይረስ ጉንፋን አምጭ ከምንላቸው ቫይረሶች አንዱ ነው፡፡ ያው አዲስ ነው ከአሁን በፊት በሰው ታይቶ አያውቅም፡፡የተለየ የሚያደርገው ከአሁን በፊት ታይቶ አለመታወቁ እንጂ ሳርስና ስዋይን ፍሉ የምንላቸው እሱን መሰል ብዙ የእርሱ ዝርያዎች አሉ፡፡ ይህ ግን በተለየ መልኩ ገዳይ ነው፡፡ በባህሪው ተላላፊ ነው አንድ ታማሚ ለብዙ ሰዎች ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ የኢቦላ በንክኪ ነው የሚተላለፈው፣ ንክኪ ከሌለ በቅርብ ርቀት ላይ ሆነህ ካልነካሃው አይተላለፍም፡፡ ኮሮና ግን አካባቢውን ራሱ በትንንሽ ድሮፕሌቶች/ እርጥበታማ ትንፋሽ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ለየት ያለ በሽታ ስለሆነ ከኢቦላ ከፍያለ የመተላለፍና የመሰራጨት ዕድል ያለው ቫይረስ ነው፡፡ ኢቦላ ገዳይ ነው፣ የመግደል ሁኔታው በጣም ከፍተኛ ነው፣ የመተላላፍ ሁኔታው ግን ያነሰ ነው፡፡ ኮሮና ደግሞ ገዳይነቱ ትንሽ ዝቅተኛ ነው፡፡ የመተላለፉ ዕድሉ ግን በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን የእኛ ቲም በየክልሉ ቲሞች/ቡድኖች አሉን አሁን ተመልሰን ከመጣን በኋላ በየስራችን ነው የገባነው፡፡ ስለዚህ ወደ 152 ሰዎች ተመዝግበዋል ለአዲሱ ለዚህ ለኮቪድ 19 ፡፡
አል-ዐይን፡ ከላይ ካነሷቸው ውጭ ሁለቱ በምን ይለያያሉ?
አቶ ህንፃ፡ ኢቦላ ምልክቱ የሚለይበት እስከ 21 ቀን ሲሆን ኮቪድ 19 ደግሞ እስከ 14 ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ ሊታይ ይችላል፡፡ እስካሁን የታየውም ይሄው ነው፡፡ ኮሮና አብዛኛውን ጊዜ የሚያጠቃው በእድሜ የገፉ ታማሚዎችን ነው፡፡ ኢቦላ ኢንፌክሽን ካለ ህጻን፣ ሴት አይልም ቅድመ ሁኔታዎችም የሉትም፡፡ ምልክታቸውም የተለያየ ነው፡፡ ትኩሳት አለ፡፡ ይሄኛው የጉንፋን አይነት ምልክት ነው ያለው፡፡ ያኛው ደሞ የተለየ ነው ማለት ነው፡፡
አል-ዐይን፡ አሁን ኢትዮጰያ ውስጥ በተከሰተው ኮሮና ቫይረስ/ ኮቪድ 19 በመከላከል ረገድ ክልል ላይ ያላችሁ ተሳትፎስ ምን ይስላል?
አቶ ህንፃ፡ እንግዲህ እንደነገርሁህ ወደ ምእራብ አፍሪካ የሄደው ቲማችን/ቡድናችን የተዋቀረው ከሀገር አቀፍ ጥሪ ተደርጎ ከመላ ሀገሪቱ በፍላጎት ክልሎችም ፈቅደው ነው የመጡት፡፡ ከዘመቻ ሲመለሱም ወደ ስራ ቦታቸው ተመልሰዋል፡፡ በተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና በግል የሚሰሩም አሉ፡፡ ለቲሙ አባላት ጥሪ አቅርበናል፡፡ በአፍሪካ ህብረት አፍሪካ ሀልዝ ቮለንቲር ኮርፕስ የሚባል አለ በሱ በኩል ለቲሙ ጥሪ ቀርቧል፡፡ መዝገባም አድርገናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትና ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያለውን ልምድ መጠቀም እፈልጋለሁ ስላለ ጥሪ አቅርቡልን ብሎ ጥሪ አቅርበን ምዝገባ አካሂደናል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በሉበትም ሆኖ ስራ እያገዙን ነው፡፡ አብዛኞቹን በክልል የሚገኙ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት የሚያግዙት እዛ የነበሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ በጎ ፈቃደኞች እየሆኑ ነው ያሉት፤እኔም በብሄራዊ ታስክ ፎርስ ውስጥ ሆኜ እየሰራሁ ነው፡፡ የተለያዩ ስብሰባዎች ሲኖሩ ሀሳብ እንሰጣለን፡፡ ከዛ ባለፈ መንግስት የሚሰጠውን መመሪያ በደንብ እያስፈጸምን ነው፡፡ እዛ የነበረውን አደረጃጃት እያስተካከል ነው፡፡ እንዴት መቀናጅ አለበት የሚለውን እያየን ነው፡፡
አል-ዐይን፡ የኢትዮጵያ የጤና ስርአት እንዲህ አይነት ወረርሽን በሚከሰትበት ጊዜ ምላሽ ለመስጠት የሚስችል አቅም አለው ወይ? ኮሌራ ተፈጥሮ ነበር ነገር ግን ይሄ ከፍ ይላል?
አቶ ህንፃ፡ አዎ… እንግዲህ እውነት ለመናገር በደንብ ከተሰራበት ከማንም አናንስም፡፡ ከሎሎች አፍሪካ ሀገራት የተሻለ አቅም ነው ያለው፡፡ በሰው ሀይልም በጤና መሰረተ ልማት እና በአቅርቦትም ቢሆን የተሻለ ነው፡፡ ሌሎች ሀገሮች ያላየ እንትን/ደካማ ሊልህ ይችላል ግን ላይቤሪያን አይተናል፡፡ ጋና፣ ናይጀሪያ፣ሴራሊን፣ ጊኒ የሚባሉ ሀገራት አይተናል፡፡ ማህበረሰቡን በሚገባው ቋንቋ ኮሙኒኬት ካደረግነው ሊረዳ ሚችል ማህበረሰብ ነው፡፡ ያው የተለያዩ ባህላዊ አመለካከቶች ሊኖሩ ይችላሉ ግን እነሱን ሰብሮ በሚመስለው በሀይማኖት አባቶች በደንብ ከተገባበት ይህን በሽታ በቀላሉ መቆጣጠር ይችላል፡፡ እውነት ለመናገር ያናጋዋል[የጤና ስርአቱን] ጣሊያንን ያናጋ በሽታ እኛን ምን ሊያደርገን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ግን እዛ ከመድረሱ በፊት ኬዞቹ በደንብ ሳይሰራጩ በማህበረሰብ ውስጥ እንዲተላለፍ ጊዜ ካልሰጠነው መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ካዛ ባለፈ ግን መዘግየት ካለ፤ ህዝባዊ ስብሰባዎች ካልቀሩ መዘግየት ካለ የጤና ስርአቱ መሽከም ይችላል ብየ አላስብም፡፡
አል-ዐይን፡ በኢትዮጵያ እስከአሁን ቫይረሱ የተገኘበት 12 ሰው ነው፤ ይህ ቁጥር ወካይ ነው ወይ? በመመርመር ሂደት ያጋጠመ የህክምና መሳሪያ እጥረት የለም ወይ?
አቶ ህንፃ፡ የሎጂስቲክ እጥረት ይኖራል፡፡ ግን ያልታመመ ሰው ሚስ ዩዝ የሚያደርገው አለ፡፡ ማስክ ያለአግባብ መጠቀም አለ፡፡ ፌስ-ማስክ ከምንም አይከላከልም ዝምብሎ ማድረግ አለ፡፡ መልበስ ያለበት ማን ነው የት ቦታ ነው የሚለበሰው የሚለው መታሰብ አለበት፡፡ ይሄ ለባለሙያው እጥረት ይፈጥራል፡፡ ማስክ የሚደረገው አንድሰው ከታማሚ ጋር ንክኪ ካለው፣ ጉንፋን ከያዘው፤ ሰው የበዛበት አካባቢ ከሄደ፣ ከተጠርጣሪ ጋር ንክኪ ካለው ብቻ ነው፡፡ ሌላው ግን ላብራቶሪ ቴስት ኪት ብዙ እጥረት አይኖርም፡፡
አል-ዐይን: ኬዝ ደፊኒሽን ምንድነው?
አቶ ህንፃ፡ ኬዝ ደፍኔሽን ማለት ኮሮና ቫይረስ ምንድነው፣ ምን ምልክቶችን ሲያሳይ ነው የምትጠረጥረው የሚለውን የሚያሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ደረቅ ሳል፣ የጉሮሮ ድርቀትና ትኩሳት ሲያሳይ፣ አሁን ደግሞ ሌሎች ምልክቶች ኬዝ ደፊኒሽን ውስጥ ገብተዋል፡፡ የ“ሎስ ኦፍ ቴስት” ማለትም የጣዕም መጥፋት ካለ እና የአፍንጫ የማሽተት አቅም ከቀነሰ አዲስ የቫይረሱ ምልክቶች ናቸው፡፡
አል-ዐይን : መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በርካታ እርምጃዎች ወስዷል፤ እርምጃዎቹ ውጤታማ ናቸው ብለው ያስባሉ?
አቶ ህንፃ፡ እየተስተዋለ ያለው ማህበረሰባዊ መራራቅ እየተተገበረ አይደለም፡፡ በየአካባባው ትልልቅ ስብሰባዎች እየተካሄዱ ነው፤ ለጊዜው ቀላል ሊመስሉ ይችላሉ ግን ኬዝ እየሆኑ ሲመጡ በጣም ፈታኝ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ አንድ እንኳን ኬዝ ከተገኘ ኮንታክት ትሬሲንግ እዛ የተሰበሰቡ ሰዎችን ቤተሰቦቻቸው የተገናኗቸው ሰዎችን በመለየት ትሬስ ለማድረግ ስለሚከብድ ፈታኝ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ ይህ መንግስትን ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍሉታል፡፡
አል-ዐይን፡ ኬዝ/ኮንታክት ትሬሲንግ እንዴት ውጤታማ ሊሆን ይችላል፤ አፍሪካ ውስጥ ድክመት እንዳለ ይነገራል?
አቶ ህንፃ፡ ላይቤሪያ ላይ ያጋጠመንን ልንገርህ ፡፡ መጀመሪያ እንደነገርኩህ ሰዉ አላመነበትም ነበር፡፡ ይሄ የእኛ አይደለም ይሄ የአሜሪካ በሽታ ነው እዚህ የሚመጡት ሆን ብለው “ዲኒያል” ነገር ነው ብለው ነበር የሚያምኑት፡፡ በዚህ ኮንታክት ትሬስ ማድረግ አልተቻለም ነበር፡፡ ማህበረሰቡ ውስጥ ሄደው ይደበቃሉ ብዙ ችግሮች ሲያጋጥሙን ነበረ ግን ምንድነው ያደረግነው የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ነው ያሳተፍነው፡፡ ማህበረሱ ውስጥ የተደበቁ ሰዎችም ካሉ ተደማጭነት ያላቸውን ሰዎች እንጠቀም ነበር፡፡ ስለዚህ በባለሙያ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና የጤና ሚኒስቴርን የሚያስተባብር አንድ ግብረ ሀይል ነበር፡፡ የአፍሪካ ህብረት፣ የአለም ጤና ድርጅትና የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከልም የግብረኃይሉ አካል ነበሩ፡፡ ተቀናጅተን ነው ኮንታክት ትሬስንግ ስንሰራ የነበረው፤ስለዚህ እዚህ ሀገርም በዚህ መልኩ ነው ተቀናጅተን መስራት ያለብን፡፡
አል-ዐይን፡ በምን ፍጥነት ነው ኢትዮጵያ መቆጣጠር የምትጭለው፤ ለመቆጣጠር እስካሁን ከወሰደቻቸው እርምጃዎች በተጨማሪ ምን መውሰድ አለባት?
አቶ ህንፃ፡ ይህን ለመገመት በጣም ያስቸግራል፡፡ ይህ የሚወሰነው እንደመንግስት እንደ ህዝብ በምንወስደው እርምጃ ነው፡፡ በሽታ እኮ ያልቃል በራሱ ይሄዳል፤ኢፒዲሞሎጅካል ፕሮሰሱን ጨርሶ ራሱ ይሄዳል፡፡ ግን ራሱ ሲጨርስ ብዙ ህዝብ ጨርሶ ነው የሚሄደው፡፡ ነገርግን ቁልፍ ቁልፍ የሚባሉ ኢንተርቬንሽኖችን ብዙ ጥፋት ሳያጠፋ መከላከል እንችላለን፡፡ በዋናነት ከጤና ጥበቃ የሚሰጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ ካደረገን ፤ መንግስት ደግሞ ያሉትን መሰረተ ልማቶች በደንብ አበልጽጎ ታማሚዎችን በደንብ ማከም፤ ኬዞችን በደንብ እየለየ ከሄደ ቶሎ እንቆጣጠረዋለን፡፡ አሁን ባለው እንዝህላልነትና መዘናጋት ከቀጠልን ግን እነ ጣሊያን ሌሎችም ያጋጠማቸው ያለ ችግር ላለማጋጠሙ ምንም ዋስትና የለንም፡፡ ሁሉም የጤና መመሪያዎች ከሃይሞኖትና ከፖለቲካ ምንም ግንኙነት ስለሌላቸው ህብረተሰቡ ተግባራዊ ሊያደርጋቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ወረርሽኑን ለመከላከል በጋራ የምንጠቀምበቸውን ተቋማት ማቆም ግድ ነው፡፡
አል-ዐይን፡ ቫይረሱ ከአዲስ አበባ ወጥቶ እንዳይዛመት ምን ይደረግ?
አቶ ህንፃ፡በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ አዲስ አባባ የወረርሽኙ ማዕከል ነው፡፡ ኬዞቹ እዚህ ስላሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ወደ ክልሎች እንዳይዛመት ክትትል እየተደረገ ነው፡፡ በክልሎች ታስክ ፎርሶች ተቋቁመዋል፡፡ በኤርፖርትና በየብስ መመርመሪያ መሳሪያዎችና የጤና ቡድኖች ተሰማርተዋል፡፡ ተጠርጣሪ ሲኖር ትራክ ያደርጋሉ፡፡ ግን አሁንም የአዲስ አባባ ሁኔታ ይወስነዋል፤ አዲስ አባባ ኬዝ የሚበዛ ከሆነ አዲስ አባባ ሎክ/መዝጋት ያስፋልጋል፡፡ አዲስ አባባን ሙሉ በሙሉ ከክልሎች እንዳይገናኝ በመዝጋት ሰው ቤቱ እንዲቆይ በማድረግ እዚህ ያለውን ኬዝ እዚሁ ኮንቴን/በመግታት ወደ ክልሎች እንዳይዛመት ማደረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አልፎ ክልል፣ ከክልል ወደ ዞን… ወረዳ እያለ የሚስፋፋ ከሆነ አደጋውን መቆጣጠር አይቻልም፡፡ ኬዙ ፍሌር/በከፍተኛ ፍጥነት የሚያድግ ከሆነ ሎክ አዲስ አባባ ሎክ ትደደጋለች፡፡ ነገርግን ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖው ግን በጣም ከባድ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ የሚወስን አይደለም፤ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎቸ የማይቋረጡበትን ሁኔታ አይቶ ሎክ ማድረግ ይቻላል፡፡