ኢራን ያጣቻቸው ዲፕሎማት - ሆሴን አሚርአብዶላሂያን
አሜሪካና እስራኤልን በጠንካራ ቃላት በመቃወም የሚታወቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካ ጋር የሚደረገውን ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ሲመሩ ቆይተዋል
ኢራን ከሳኡዲ አረቢያ ጋር ግንኙነቷን ስታድስም አሚርአብዶላሂያን ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል
ኢራን ለውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ መፈጸም በትጋት የሰሩትን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ሆሴን አሚርአብዶላሂያን አጥታለች።
ሚኒስትሩ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ህይወት በቀጠፈው የሄሊኮፕተር አደጋ ነው ህይወታቸው ያለፈው።
የቀድሞው ወታደር፤ ለኢራን አብዮታዊ ዘብ ቅርበት ያላቸው፤ ምዕራባውያንን በጠንካራ ቃላት ሸንቆጥ የሚያደርጉት ሆሴን አሚርአብዶላሂያን ለዲፕሎማሲያዊ ንግግርም ዝግጁ ነበሩ።
አሜሪካ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ዘመን ከኢራኑ የኒዩክሌር ስምምነት ከወጣች በኋላ የሀገራቱ ግንኙነት እየሻከረ ሲሄድም ሚኒስትሩ ዋሽንግተንን የሚኮንኑ ንግግሮችን ከማድረግ ባሻገር ሀገራቱ የሚያካሂዱትን ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ይከታተላሉ።
ኢራን በቻይና አደራዳሪነት ከሳኡዲ አረቢያ ጋር ግንኙነቷን ስታድስም የአሚርአብዶላሂያን ሚና ከፍተኛ እንደነበር አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
ሆሴን አሚርአብዶላሂያን ከ2011 እስከ 2013 አሊ አክባር ሳሌህ በሚመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አገልግለዋል።
ከአሜሪካ ጋር የኒዩክሌር ስምምነት ሲደረስ ቁልፍ ድርሻ በነበራቸው ሞሀመድ ጃቫድ ዛሪፍ የስልጣን ዘመንም በዲፕሎማትነት ቢያገለግሉም ከዛሪፍ ጋር በኢራን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዙሪያ ልዩነት ነበራቸው።
የወቅቱ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀመድ ጃቫድ ዛሪፍ አሚርአብዶላሂያንን የኦማን አምባሳደር እንዲሆኑ ያቀረቡላቸውን ጥያቄ ሳይቀበሉት መቅረታቸውም ይነገራል።
አሚርአብዶላሂያን ዳግም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተመለሱትና ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት በ2021 ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ተመርጠው ስልጣን ሲይዙ ነው።
የኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ተተኪ ይሆናሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩት ኢብራሂም ራይሲ የውጭ ጉዳዩን እንዲመሩ የመረጧቸው ሆሴን አሚርአብዶላሂያን አላሳፈሯቸውም።
በ2022 በማሻ አሚኒ ግድያ ምክንያት ተቃውሞ ሲበረታባቸውም ሆነ እስራኤል በጋዛ ጦርነት ስትከፍት የኢራን መንግስትን አቋም በሚገባ ሲያንጸባርቁ ቆይተዋል።
የፍልስጤማውያን እልቂት እንዲቆም ከተለያዩ ሀገራት ባለስልጣናት እና ከሃማስ አመራሮች ጋር ከመምከር ባለፈም እስራኤል ላይ የአጻፋ እርምጃ እንደሚወሰድ ዝተው ቴህራን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቴል አቪቭ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏ ይታወሳል።
ኢራን እና ፓኪስታን ከወራት በፊት የገቡበትን ፍጥጫ በዲፕሎማሲያዊ ንግግር በማርገብም ትልቅ ድርሻ ነበራቸው።
ዲፕሎማሲ ከሃይል እርምጃ ጋር ይቀናጃል ብለው የሚያምኑት ሆሴን አሚራብዶላሂያን በ60 አመታቸው ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፥ የሁለት ልጆች አባት ነበሩ።