የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ወደ ኒጀር ወታደሮቻቸውን ለማዝመት የሚያስችላቸውን እቅድ አጠናቀቁ
የሀገራቱ የጦር አመራሮች በናይጀሪያ አቡጃ ባደረጉት ምክክር ነው ከስምምነት ላይ የደረሱት
ኢኮዋስ ፕሬዝዳንት ሞሀመድ ባዙም እንዲለቀቁ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ነገ ይጠናቀቃል
የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ኒጀር በሚልኩበት ሁኔታ ላይ በዝርዝር መክረው ከስምምነት መድረሳቸው ተነገረ።
የሀገራቱ መከላከያ ለሁለት ቀናት በናይጀሪያ አቡጃ ባደረጉት ምክክር ወታደራዊ ጣልቃገብነቱ በሚፈጸምበት ዝዝርዝር ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
በዚህ ምክክር ላይ የማሊ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒ እና ኒጀር የመከላከያ ሚኒስትሮች አልተሳተፉም።
በአቡጃ በተደረገው የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) አባል ሀገራት የጦር አመራሮች ውይይት በቀጣይ በኒጀር ስለሚካሄድ ዘመቻ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የኢኮዋስ የፖለቲካ፣ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አብደል ፋቱ ሙሳህ፥ በኒጀር ለሚደረገው ዘመቻ የሚያስፈልገው ወታደራዊ ሃይል እና ግብአት እንዲሁም ጊዜው ላይ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
የወታደራዊ አመራሮቹ የተስማሙበትን የጣልቃመግባት እቅድ የሀገራቱ መሪዎች ፊርማቸውን ሊያኖሩበት እንደሚገባም ነው ያነሱት።
ኮሚሽነሩ የኢኮዋስ ጥምር ሃይል መቼ ወደ ኒያሚ እንደሚዘልቅ ባይጠቅሱም የመንግስት ግልበጣውን ያደረገው ጁንታ በቀጣይ ቀናት ስልጣኑን ለፕሬዝዳንት ባዙም እንዲመልስ አሳስበዋል።
የኢኮዋስ መሪዎች ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ስብሰባ ወታደራዊ ሃይሉን ወደ ስልጣን እንዲመልስ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ ነገ ይጠናቀቃል።
በጀነራል አብዱርሃማን ቲያኒ የሚመራው ወታደራዊ ሃይል ግን የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ከመግባት ሊቆጠቡ ይገባል ሲል አስጠንቅቋል።
“በኒጀር ላይ ለሚታወጅ ወረራ ፈጣን አጻፋዊ እርምጃ እንወስዳለን” ያሉት የወታደራዊ ሃይሉ ቃል አቀባይ ኮሎኔል አማዱ አብድራማን፥ ወታደር በሚልኩት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ዜጎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ዝተዋል።
በማሊ እና ቡርኪናፋሶ የተደረጉ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎችን ማክሸፍ ያልቻለው ኢኮዋስ በኒጀር ይሳካለት ይሆን ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው።