ፈረንሳይ ከ260 በላይ የተለያዩ ሀገራት ዜጎችን ከኒጀር አስወጣች
ከኒያሚ ወጥተው ፓሪስ ከገቡት ፈረንሳውያን በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን፣ ናይጀሪያውያን እና ሊባኖሳውያን ይገኙበታል
ኒጀር ከአምስት ሀገራት ጋር የሚያዋስናትን ድንበር መክፈቷ ተነግሯል
ፈረንሳይ ባለፈው ሳምንት የመንግስት ግልበጣ ከተደረገባት ኒጀር ዜጎቿን ማስወጣት ጀምራለች።
262 ፈረንሳውያንን እና የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ዜጎችን የጫነው አውሮፕላን ዛሬ ማለዳ ፓሪስ መግባቱንም የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪና ኮሎና ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
ከኒያሚ ወጥተው ፓሪስ ከደረሱት ውስጥ ኢትዮጵያውያን፣ የፖርቹጋል፣ ናይጀሪያ እና ሊባኖስ ዜጎች እንደሚገኙበትም ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።
ከኒጀር ለመውጣት ፍላጎት ያላቸውን ፈረንሳውያንን እና የተለያዩ ሀገራት ዜጎችን የሚያስወጡ ሁለት አውሮፕላኖች ለጉዞ መዘጋጀታቸውም አብራርተዋል።
የመንግስት ግልበጣውን ያደረጉት ሃይሎች ደጋፊዎች በኒያሚ ፈረንሳይን የሚያወግዙ ሰልፎችን ማድረጋቸውና ኤምባሲዋን መደብደባቸው ይታወሳል።
ፓሪስ ወታደራዊ ጣልቃገብነት ልትፈጽም እንደምትችልም የመንግስት ግልበጣውን ያደረጉት ሃይሎች ሲያነሱ ይሰማል።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግን በቀድሞ ቅኝ ግዛቷ ኒጀር ከ1 ሺህ 500 በላይ ወታደሮች ያሏት ፓሪስ ቅድሚያ የምትሰጠው ለዜጎቿ ደህንነት መሆኑን በመጥቀስ ስጋቱን አጣጥለውታል።
በተያያዘ ኒጀር ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ባዙምን ከስልጣን ያነሳው መፈንቅለ መንግስት አንደኛ ሳምንቱን ሲይዝ ከአምስት ሀገራት ጋር የሚያዋስናትን ድንበር መክፈቷ ተነግሯል።
ኒያሚን ከአልጀሪያ፣ ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሊቢያ እና ቻድ የሚያዋስነው የየብስ ድንበርና የአየር ክልሉ ዳግም መከፈቱን ወታደራዊ ሃይሉ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
መፈንቅለ መንግስቱን ያካሄደው ሃይል ስልጣኑን ካላስረከበ ጦር እንደሚያዘምት የዛተው የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) አባል ሀገራት ወታደራዊ መሪዎች ከዛሬ ጀምሮ በናይጀሪያ አቡጃ ይመክራሉ ተብሏል።
እስከ ፊታችን አርብ በሚዘልቀው ስብሰባ በቀጣይ ኢኮዋስ የሚወስደው እርምጃ ላይ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ይጠበቃል።
የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች ባለፈው እሁድ ባደረጉት ስብሰባ ወታደራዊ ሃይሉ በአንድ ሳምንት ውስጥ ስልጣኑን ለፕሬዝዳንት ሞሃመድ ባዙም እንዲመልስ ማሳሰባቸውና ማዕቀብ መጣላቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ባዙም ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በጀነራል አብዱራህማን ታኒ በሚመራው ጁንታ መታፈናቸውና ከስልጣናቸው በሃይል መነሳታቸው አይዘነጋም።