በማሊ ጁንታ ላይ ተጽእኖ ይፈጥራል የተባለው የተመድ የፀጥታው ም/ቤት ልዑክ ባማኮ ገባ
ማሊ “የልዑካኑ መምጣት ለሀገሪቱ ያለንን ቀናኢ ራዕይ የምናሳውቅበት ጥሩ አጋጠሚ ነው” ብላለች
የልዑኩ ወደ ባማኮ ማቅናት የማሊ ሁኔታ በሚገባ ለመረዳት መፍትሄ ለመሻት ጥሩ ግብአት ይሆናል ተብሏል
በአሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና ኒጀር አምባሳደሮች የተመራውና የማሊው ጁንታ ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲጀምር ተጽእኖ ይፈጥራል የተባለለትየተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ልዑክ ባማኮ መግባቱ ተሰምቷል።
ልዑኩ በዘጠኝ ወራት ሁለት መፈንቅለ መንግስታት ባስተናገደቸው ማሊ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ በማሊ ወታደራዊ ኃይል ከሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በዴሞክራሲያዊ ሂደት ዙርያ ይመክራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፈረንሳዩ የዜና ወኪል /ኤኤፍፒ/ ዘግቧል።
የልዑኩ ወደ ባማኮ ማቅናት የምዕራብ አፍሪካ መንግስታት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ/ኢኮዋስ/ ባስቀመጠው መሰረት ማሊ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንድታካሂድ “ቸልተኝነት እያሳየ ባለ የማሊ ጁንታ ላይ ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ እንዲፈጥር ዕድል የሚፈጥር ነው”ም ነው የተባለው።
በተባበሩት መንግስታት የኬንያ አምባሳደርና የልዑኩ አባል ማርቲን ኪማኒ፤ የልዑኩ ወደ ማሊ ማቅናት በሀገሪቱ ውስጥ ስላለው ሁኔታ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።
የማሊን ሁኔታ በሚገባ መረዳት በኒውዮርክ ለሚደረገው ውይይትና መፍትሄ ለመሻት ጥሩ ግብአት እንደሚሆንም አምባሳደሩ አክለው ገልፀዋል።
ከወታደራዊ ኃይሉ ጋር የሚደረገው ውይይት ሁኔታውን ለመረዳትና የመንግስትን ሪፖርት ለመስማት ጥሩ አጋጣሚ ነው ያሉት ደግሞ ልዑኩን የተቀበሉት የማሊ የውጭ ጉዳዮች እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒሰትሩ አብዶላየ ዲዮፕ ናቸው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ"ልዑኩን በደስታ ነው የተቀበልነው፤ ይህ አጋጣሚ የማሊ ነባራዊ ሁኔታን ለማስረዳት የምንጠቀምበትም ነው፤ በሽግግር መንግስቱ ስለተከናወኑ ተስፋ ሰጪ ተግባራት፣ ቀጣይ ራዕያችን እንዲሁም ለማካሄድ ስላቀድነው ግልጽና ተአማኒ ምርጫ የምናሳውቅበት ይሆናል"ም ብለዋል።
ሂውማን ራይትስ ዎች ዓርብ ባወጣው መግለጫ ወደ ባማኮ ያመራው ልዑክ የማሊ ባለስልጣናትን "በማሊ የፀጥታ ኃይሎች ተፈጽመዋል የተባሉትን ግድያዎች፣ እገታዎች እና እስራቶች" እንዲያጣሩ የሚያበረታታበት አጋጣሚ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳለው መግለጹ ይታወሳል።
የ38 ዓመቱ ኮለኔል አስሚ ጎይታ ካሳለፍነው ግንቦት ወር ጀምሮ ደግሞ ጊዜያዊ አስተዳድሩን በማፍረስ እራሳቸውን የማሊ ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት አድርገው መሾማቸው ይትወሳል።
በዚህ ድርጊታቸውም አፍሪካ ሀብረትን ጨምሮ የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ማሊን ከአባልነት ማገዱንም ጭምር የሚታወቅ ነው።