ኢኮዋስ፤ መፈንቅለ መንግስት በተካሄደባቸው ሶስት የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት ላይ ጥሎት የነበረውን ዕገዳ አነሳ
ኢኮዋስ በማሊ፣ ጊኒ እና ቡርኪና ፋሶ ጥሎት የነበረውን እገዳ አንስቷል
ሆኖም ሃገራቱ አሁንም ከአባልነት እንደታገዱ ይቆያል ተብሏል
የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) የመንግስት ግልበጣ በተደረገባቸው በሶስት አባል ሃገራቱ ላይ ጥሎት የነበረውን እገዳ አነሳ፡፡
ኢኮዋስ በማሊ፣ ጊኒ እና ቡርኪና ፋሶ ጥሎት የነበረውን እገዳ ነው ያነሳው፡፡
በጋና አክራ ጉባዔውን ያደረገው ቀጣናዊው ተቋም በወታደራዊ አገዛዝ ስር በወደቁት ሃገራት ላይ ጥሎት የነበረውን ምጣኔ ሃብታዊ እገዳ ማንሳቱን አሳውቋል፡፡
ሆኖም ሃገራቱ አሁንም ከአባልነት እንደታገዱ ይቆያሉ ብሏል ኢኮዋስ፡፡ እገዳው ምርጫ እስከሚያካሂዱ ድረስ የሚዘልቅ ነው እንደ ቀድሞው የተቋሙ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት አይቮሪኮስታዊው ፖለቲከኛ ዣን ክላውድ ካሲ ብሩ ገለጻ።
የተቋሙ አባል ሃገራት መሪዎች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሃገራቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
መሪዎቹ በማሊ ወታደራዊ ጁንታ የቀረበላቸውን የሽግግር እና ምርጫ ፍኖተ ካርታ ተቀብለዋል፡፡ ፍኖተ ካርታው በኮ/ል አሲማ ጎይታ የሚመራው ወታደራዊ መንግስት ከሁለት ዓመታት በኋላ በፈረንጆቹ መጋቢት 2024 ላይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማካሄድ ውጥን እንዳለው የሚያሳይ ነው፡፡ የጊኒ እና ቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ መንግስታት ይህንኑ ማድረጋቸውም ነው የተነገረው፡፡ ሆኖም የምርጫውን ቀን በውል አላሳወቁም፡፡
ኢኮዋስ በሃገራቱ ላይ የንግድና ሌሎችንም የትራንስፖርት ግንኙነቶች አቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በዚህም ሃገራቱ ለከፋ ምጣኔ ሃብታዊ ድቀት ተዳርገው ነው የቆዩት፡፡ ሆኖም በሃገራቱ ያለው የአክራሪዎች እንቅስቃሴ እየተጠናከረ መምጣት የጣለውን እገዳ ለማንሳት ምክንያት ስለመሆኑም ነው የተነገረው፡፡
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል የቀጣናዊውን ተቋም እርምጃ አወድሰዋል፡፡