የምዕራብ አፍሪካ መንግስታት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ጊኒን ከአባልነት አገደ
በምዕራብ አፍሪካ እየተስተዋሉ ያሉ ድርጊቶች “ቀጠናው በዴሞክራሲ ያለው እምነት እየሳሳ ለመምጣቱ” ማሳያ ነው ተብሏል
የኢኮዋስ መሪዎች በቁጥጥር ስር ያሉት “አልፋ ኮንዴ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ” ጠይቋል
የምዕራብ አፍሪካ መንግስታት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ጊኒን ከአባልነት አገደ፡፡
ኢኮዋስ ጊኒን ከአባልነት ያገደው ሰሞኑን በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ላይ የተደረገውን መፈንቅለ መንግስት ተክትሎ ነው፡፡
የድርጅቱ አባል የሆኑት 15 ሀገራት መሪዎች ጊኒን በማስመልክት የበይነ መረብ ውይይት አካሂደዋል፡፡
መሪዎቹ በውይይታቸው መጨረሻ “የሀገሪቱ ህገ-መንግስት እንዲከበር እና አልፋ ኮንዴ ካለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ” ጠይዋል፡፡
በአንድ ሳምንት ውስጥ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ወደ ጊኒ አቅንቶ በጉዳዩ ላይ ይነጋገር ሲሉ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ነው የቡርኪናፋሶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልፋ ባሪ የተናገሩት፡፡
“ተልእኮው ካለቀ በኋላ ኢኮዋስ አሁን የያዘውን አቋም እንደገና የሚመረምርና የሚያጤን ይሆናል”ም ብለዋል፡፡
የጊኒ መፈንቅለ መንግስት መሪ ኮሎኔል ማማዲ ደንቦያ በጊኒ አንድነት ለመምጣት እና የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ቃል ቢገቡም መቼ እና እንዴት ስለሚለው ያስቀመጡት ግልጽ ነገር የለም፡፡
መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ ኮሎኔሉ የፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴን የህገ-መንግስት ለውጥ በመቃወማቸው የታሰሩ 80 የሚሆኑ የፖለቲካ እስረኞችን ማስፈታታቸው ይታወሳል፡፡
እንደ ፈረንጆቹ 2020 በማሊ የተደረገውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ ኢኮዋስ በሀገሪቱ የጣለውን የኢኮኖሚ ማእቀብ በጊኒ ላይ ይደግመው ይሆን ወይ ለሚለው ግን፤ ባሪ ምንም ከማለት ተቆጥቧል፡፡
አንዳንድ የምጣኔ ኃብት ልሂቃን ግን ኢኮዋስ ከጊኒ ጋር የሚኖረው ጥቅም ውስን ወይም በከፊል ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡
ሀገሪቱ የምዕራብ አፍሪካ የገንዘብ ምንዛሪ አባል አለመሆኗ እንዲሁም እንደ ማሊ ወደብ አልባ አለመሆኗ ደግሞ የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎቹ በምክንያትን የሚያስቀምጡት ነው፡፡
ከቅርብ ወራት ጊዜያት ወዲህ በምዕራብ አፍሪካ እየተስተዋለ ያለው ነገር የዴሞክራሲ አቀንቃኞች ነን በሚሉ አካላት ክፉኛ እየተተቸ እና ትኩረት እየተሰጠው ይገኛል፡፡
አክቲቪስቶች “በምዕራብ አፍሪካ እየተስተዋሉ ያሉ ድርጊቶች ቀጠናው በዴሞክራሲ ያለውን እምነት እየሳሳ መምጣቱንና ለመፈንቅለ መንግስት ትልቅ ቦታ መስጠቱ የሚያመላክት ነው” ብለውታል፡፡
ባለፈው ወርሃ ግንቦት ሌላኛዋ የምዕራብ አፍሪካ ሀገር ማሊ መፈንቅለ መንግስትማስተናገዷ የሚታወስ ነው፡፡
የማሊ የሽግግር ባለሥልጣናት በመጪው የካቲት ምርጫን ለማደራጀት ቃል ቢገቡም አኳሃናቸው አጥጋቢ እንዳልሆነ ኢኮዋስ ከቀናት በፊት አስታወቋል፡፡