ኢኮዋስ ቡርኪናፋሶን በመፈንቅለ መንግስት ምክንያት ከአባልነት አገደ
ኢኮዋስ በማሊ እና በጊኒ ላይ የጣለው ማእቀብ ሌላ መፈንቅለ መንግስት ከመከሰትም አላዳነም
የኢኮዋስ አባል ሀገራት በሚቀጥለው ሣምንት በሚሰበሰቡበት ወቅት በቡርኪናፋሶ ላይ ማእቀብ ሊጥሉ ይችላሉ ተብሏል
የምዕራብ አፍሪካው የኢኮኖሚ ብሎክ(ኢኮዋስ) ቡርኪናፋሶን ከአባልት ያገደው በሀገሪቱ በተካሄደው የመፈንቅለ መንግስት ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢኮዋስ አባል ሀገራት ከእግዱ ውጭ ምንም የተጣለ ማእቀብ አለመኖሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
- የቡርኪናፋሶ ጦር ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን ማንሳቱን አስታወቀ
- ኢኮዋስ የቡርኪናፋሶ መፈንቅለ መንግስት" የሀገሪቱን ትልቅ የዴሞክራሲ ውድቀት የሚያመለክት ነው" ሲል አውግዟል
የቡርኪናፋሶ ጦር የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ሮች ካቦሬን ከስልጣን ማስወገዱ፣ባለፉት 18 ወራት በተከታታይ ለተከሰቱት መፈንቅለ መንግስቶች ተግባራዊ ምላሽ ለሚሰጠው 15 አባል ሀገራት ላሉት ኢኮዋስ አዲስ ፈተና ሆኖበታል፡፡
ኢኮዋስ አባል ሀገራት ባወጡት መግለጫ የኢኮዋስ የመከላከያ ኃላፊ ወደ ቡርኪናፋሶ ዋና ከተማ ኡጋድጉ ያመራል ተብሏል፡፡
የኢኮዋስ አባል ሀገራት መሪዎች ወደ ቡርኪናፋሶ የተጓዘው ቡድን ምርመራ ውጤት ላይ ለመምከር ወደ ጋና ዋና ከተማ አክራ ይመራሉ፡፡ ቀድሞውንም በአማጺያን የተወጠረችውን ሀገር ወደ አለመረጋጋት ውስጥ ይከታል ብለው የሚፈሩት ኢኮዋስ እና አለምአቀፍ አጋሮቹ፤ችግሩን ለመፍታት ያላቸው አቅም ውስን ነው ተብሏል፡፡
ኢኮዋስ ቡርኪናፋሶ ላይ ማእቀብ ላለመጣል የወሰነው ውሳኔ፤ኢኮዋስ ባለፈው መስከረምና ግንቦት በማሊ እና ጊኒ በነበሩት መፈንቅለ መንግስት ወቅት ከጣለው ድንበር የመዝጋት ውሳኔ ጋር ተነጻጽሯል፡፡
ኢኮዋስ በማሊ እና በጊኒ ላይ የጣለው ማእቀብ ብዙም ለውጥ አላመጣም፤ ሌላ መፈንቅለ መንግስት ከመከሰትም አላዳነም፡፡
የኢኮዋስ አባል ሀገራት በሚቀጥለው ሣምንት በሚሰበሰቡበት ወቅት በቡርኪናፋሶ ላይ ማእቀብ ሊጥሉ ይችላሉ ተብሏል፡፡