ምክር ቤቱ ካጸደቀው ተጨማሪ በጀት ውስጥ 90 ቢሊየን ብር ለመከላከያ የተመደበ መሆኑ ተገለፀ
የ2014 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስቱ በጀት 561 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ሆኖ በምክር ቤቱ መፅደቁ ይታወሳል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ሶስተኛ ልዩ ስብሰባው የቀረበለትን የ122 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አጽድቋል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ዛሬ ባካሄደው ሶስተኛ ልዩ ስብሰባው የቀረበለትን የ122 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አጽድቋል።
በምክር ቤቱ ከጸደቀው በጀት ውስጥ 90 ቢሊየኑ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ስንቅና ትጥቅ እንደሚውል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ አስረድተዋል።
እንዲሁም ምክር ቤቱ ለዕለት ደራሽ ዕርዳታ 8 ቢሊየን ብር፣ ለመጠባበቂያ በጀት 5 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ 7 ቢሊዮን ብር እና ለታክስ ገቢ ጉድለት ማካካሻ 9 ቢሊዮን ብር አጽድቋል።
ተጨማሪ በጀቱ የተቋረጡ እና በጅምር ላይ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል እንዲሁም በጦርነቱና በኮቪድ 19 ምክንያት በቂ ያለተሰበሰበውን ታክስ ጉድልት ለመሙላት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ለመከላከያ የተመደበው በጀት ወቅታዊና ተገቢ መሆኑን የገለፁት የምክር ቤቱ አባላት፤ ለመልሶ ማቋቋም የተመደበው ገንዘብ ግን ከደረሰው ውድመት አኳያ በጣም አነስተኛ እንደሆነ አስተያየት ሰጥተዋል።
የተጨማሪ በጀት ውሳኔው በዘጠኝ ተቃውሞ በሰባት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል።
ቀደም ሲል ለ2014 በጀት አመት 561 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የፌደራል መንግስቱ በጀት ሆኖ በምክር ቤቱ መፅደቁ የሚታወስ ነው።
ምክር ቤቱ በተጨማሪነት የማኀበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለጤና፣ ማህበራዊና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።