ኢኮዋስ የቡርኪናፋሶ መፈንቅለ መንግስት" የሀገሪቱን ትልቅ የዴሞክራሲ ውድቀት የሚያመለክት ነው" ሲል አውግዟል
በቡርኪና-ፋሶ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለመምከር በሚቀጥሉት ቀናት ልዩ ስብሰባ እንሚያካሂድም ነው ኢኮዋስ የገለጸው
የቡረኪናፋሶ መፈንቅለ መንግስት የዓለም አቀፉ ማህበረስብ ትኩረት እንደሳበ ነው
የምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ማህበረሰብ (ECOWAS)በቡርኪናፋሶ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለመመከር ልዩ ስብሰባ ሊያካሂድ ነው፡፡
በቡርኪናፋሶ የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት መመካሄዱን ተከትሎ “በሀገሪቱ ያለውን ሁኔታ መመርመር የቀጠናው አባል ሀገራት ዋና አጀንዳ እንደሚሆን” ኢኮዋስ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ኢኮዋስ “ከቀጠናው እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኩል በሀገሪቱ መረጋጋት እንዲኖርና እና ህገ-መንግስታዊ ስርአት እንዲከበር ጥሪ ቢደረግም፤ ሰኞ ጥር 24 ቀን 2022 በተደረገው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ፕሬዝዳንት ሮች ካቦሬ ከስልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ በቡርኪና ፋሶ ያለው ሁኔታ አሳስቦኛል”ም ብሏል፡፡
ኢኮዋስ መፈንቅለ መንግስቱ "የቡርኪናፋሶን ትልቅ ዲሞክራሲያዊ ውድቀት የሚያመለክት ነው" ሲልም አውግዞታል፡፡
የደቡብ አፍሪካ መንግስት ማክሰኞ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ለተፈጠሩ ችግሮች ሰላማዊ መፍትሄ ማበጀት ይገባል ሲል የኢኮዋስን አቋም እንደሚጋራ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
“ወታደራዊ እርምጃ በፍፁም መፍትሄ ሊሆን አይቻልም፣ ግጭቶችን ለመፍታት እና ዘላቂ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ብቸኛ መንገዶች ውይይት እና ድርድር ብቻ ናቸው”ም ነው ያለው የደቡብ አፍሪካ መንግስት በመግለጫው።
የቡርኪናፋሶ ጦር ሀገሪቱን ሲመሩ የቆዩትን ፕሬዝዳንት ሮች ካቦሬን በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ማንሳቱን በትናትናው እለት ይፋ ማደረጉ ይታወሳል፡፡
ጦሩ ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን ከማስወገዱም በላይ ሕገ መንግስቱም አገልግሎት ላይ እንዳይውል መታገዱንም አስታውቋል፡፡ የቡርኪናፋሶ ካቢኔ እንዲፈርስ መወሰኑን እና ሀገሪቱ ከጎረቤቶቿ ጋር የምትዋሰንባቸው ሁሉም ድንበሮች መዘጋታቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የባህር በር የሌላት ቡርኪና ፋሶ ከፈረንሳይ የቅኝ ግዛት ቀንበር ከተላቀቀችበት ከአውሮፓውያኑ 1960 ጀምሮ በርካታ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች ያስተናገደች ሀገር ናት፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፕሬዝዳንት ካቦሬ በጦሩ መታሰራቸው እንዳሳሰበው ገልጾ፤ ከታሰሩበት እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡ ፕሬዝዳንት ሮች ካቦሬ አሁን የት እና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እስካሁን አልታወቀም ተብሏል፡፡
ዋሸንግተን በቡርኪናፋሶ ያለውን ነገር “ይህ ነው” ለማለት ገና መሆኑንም ገልጻለች፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ይህንን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ማውገዛቸውን ጽ/ቤታቸው ገልጿል፡፡
የተመድ ዋና ጸሀፊ ቃል አቀባይ እንዳሉት የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች ጠብመንጃቸውን እንዲያስቀምጡ ጉተሬዝ ጠይቀዋል፡፡
ባለፉት 18 ወራት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት በሆኑት ማሊ እና ጊኒ መፈንቅለ መንግስት ተካሂዶ የየሀራቱ ጦር በትረ ሰልጣን ጨብጧል፡፡