ጦሩ፤ መፈንቅለ መንግስቱ ያለምንም ችግር ተከናውኗል ብሏል
የቡርኪናፋሶ ጦር ዛሬ ሀገሪቱን የቆዩትን ፕሬዝዳንት ሮች ካቦሬን በመፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ማንሳቱን ይፋ አደረገ፡፡
ጦሩ ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን ከማስወገዱም በላይ ሕገ መንግስቱም አገልግሎት ላይ እንዳይውል መታገዱንም አስታውቋል አሁን ላይ የቡርኪናፋሶ ካቢኔ እንዲፈርስ የተወሰነ ሲሆን ሀገሪቱ ከጎረቤቶቿ ጋር የምትዋሰንባቸው ሁሉም ድንበሮች መዘጋታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የባህር በር የሌላት ቡርኪና ፋሶ ከፈረንሳይ የቅኝ ግዛት ቀንበር ከተላቀቀችበት ከአውሮፓውያኑ 1960 ጀምሮ በርካታ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች ተደርገውባታል ተብሏል፡፡ ወርቅ አምራቿ፤ ነገር ግን ድሃዋ ቡርኪና ፋሶ ዛሬ ቤተ መንግስቷ በወታደሮች ቁጥጥር ስር ግብቷል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፕሬዝዳንት ካቦሬ በጦሩ መታሰራቸው እንዳሳሰበው ገልጾ፤ ከታሰሩበት እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡ ፕሬዝዳንት ሮች ካቦሬ አሁን የት እና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እስካሁን አልታወቀም ተብሏል፡፡ ዋሸንግተን በቡርኪናፋሶ ያለውን ነገር “ይህ ነው” ለማለት ገና መሆኑንም ገልጻለች፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ይህንን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ማውገዛቸውን ጽ/ቤታቸው ገልጿል፡፡ የተመድ ዋና ጸሀፊ ቃል አቀባይ እንዳሉት የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች ጠብመንጃቸውን እንዲያስቀምጡ ዋና ጸሐፊው ጠይቀዋል፡፡
ጦሩ ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን ያነሳው በሀገሪቱ የጸጥታ ችግሮች በመባበሳቸው እና ካቦሬ ቡርኪናፋሶን አንድ ማድረግ አልቻሉም በማለት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ ባለፈም ካቦሬ ለጸጥታ ችግር የሆኑ ሰርጎ ገቦችን በተገቢው መጠን አልተከላከሉም በሚልም እንደሆነ ተገልጿል፡፡ የቡርኪናፋሶ መፈንቅለ መንግስት መሪዎች ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን የማንሳቱ ሂደት ያለምንም ግጭት መከናወኑን አስታውቀዋል፡፡
ባለፉት 18 ወራት የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት በሆኑት ማሊ እና ጊኒ መፈንቅለ መንግስት ተካሂዶ የየሀገሮቹ ጦር ስልጣን ተቆጣጥሯል፡፡