መንግስት የዜጎችን ደህንነት እንዲያስጠብቅ ኢዜማ አሳሰበ፡፡
ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ መሆኑን የሚያረጋግጥ የምዝገባ ምስክር ወረቀት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተቀበለው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን ደህንነት እንዲያስጠበቅ ጠይቋል፡፡
ፓርቲው ዛሬ ጥር 22 ቀን 2012 ዓ.ም በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በቅርቡ ከደምቢ ዶሎ ዩኒቭርሲቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ በጉዞ ላይ ሳሉ ማንነታቸው ባልታወቁ ሃይሎች የታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ፣ የ 2012 ዓ.ም ምርጫና ሌሎች ጉዳዮችም በመግለጫው ተካተዋል፡፡
የታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ
በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ላይ የተደረገው እገታ መንግሥት የተማሪዎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ ያለመወጣቱ ማሳያ ነው ያለው ፓርቲው፣ አሁንም ቢሆን መንግስት ተማሪዎቹን ከእገታ የማስለቀቁን ኃላፊነት በአግባቡና በፍጥነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዱአለም አራጌ የታገቱት ተማሪዎች የአንድ ክልል አሊያም የአንድ አካባቢ ጉዳይ ብቻ ሆኖ መታየት የለበትም ብለዋል፡፡ ጉዳዩ ሀገራዊ እንደመሆኑ ድርጊቱን መላው ኢትዮጵያውያን ሊያወግዙ ይገባል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎቹ እንዲለቀቁም ሁሉም አካላት የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ እንዳለባቸው የገለጹት አቶ አንዱአለም በተለይ ተማሪዎቹ የታገቱበት አካባቢ ማህበረሰብ አባላት ጉዳዩን በሚገባ በመከታተል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
በአጠቃላይ መንግስት ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚሠጠው ትኩረት ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየና ከወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት የሚጠብቃቸው መሆን እደሚገባው ያሳሰበው ፓርቲው በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች ባሉ ዩኒቨርስቲዎች የተከሠቱ ችግሮች የሕዝብን ልብ ሰብረው ያለፉ ናቸው ብሏል፡፡
ከደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ክስተት ጋር በተያያዘ፣ መንግሥት ስለተማሪዎቹ እገታ ወቅቱን የጠበቀ እና ትክክለኛ መረጃ ለተማሪዎቹ ቤተሰቦች እና ለሕዝብ እንዲሰጥ ኢዜማ ከዚህ በፊት መጠየቁ ይታወሳል፡፡ ይሁንና መንግሥት ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ የመስጠት ከፍተኛ ክፍተት ነበረበት ያለው መግለጫው መንግሥት ተማሪዎቹን ከእገታ የማስለቀቁን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ እና ህዝብን ከስጋት እንዲያላቅቅ ጠይቋል፡፡
የህግ የበላይነት
የትኛውም በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀስ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ተግባር የኢትዮጵያን ሕግ እና ያፀደቀቻቸውንና የተቀበለቻቸውን ዓለማቀፍ ድንጋጌዎች ባከበረ መልኩ ብቻ እንዲሆን መንግስት መስራት አለበት ሲልም ፓርቲው አሳስቧል፡፡
ዜጎች በሕግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ካልተረጋገጠላቸው እና ከሕግ በታች መሆናቸውን ካልተረዱ ማንም እየተነሳ የፈለገውን አድርጎ ‹‹አልጠየቅም›› የሚል ማን አለብኝነት ከሠፈነ ሀገሪቱ ማቆሚያ ወደሌለው ሁከት እንዳትገባ እንደሚሰጋም ነው የተገለጸው፡፡በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ ህግን ብቻ አክብሮ እንዲንቀሳቀስ እና ዜጎች በሕግ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ነው ኢዜማ ያሳሰበው፡፡
ኢዜማ መንግስት ጸጥታ ማስከበር እየቻለ ነግር ግን ቸልተኝነት አሳይቷል ሲል ከሰሞኑ መግለጫ ሰጥቶ የነበረው ኢዴፓ ደግሞ በተቃራኒው መንግስት በሀጋሪቱ ጸጥታን ለማረጋገጥ አቅም የለውም ይላል፡፡
ምርጫ 2012 ዓ/ም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሀገራዊው ቀጣይ ምርጫ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲደረግ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
ይህንን ተከትሎ በሀገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ምርጫ ይደረግ አይደረግ በሚል እየተከራከሩ ናቸው፡፡ ምርጫ ይደረግ የሚሉት ፓርቲዎች ሀገሪቱ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ያስፈልጋታል፤ አሁን ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘንድሮ የስራ ዘመኑ ስለሚያበቃ ምርጫው የግድ ነው የሚል የህግ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡
ምርጫው መደረግ የለበትም የሚሉት ደግሞ የሀገሪቱን የጸጥታ ችግር በምክንያትነት ያነሳሉ፡፡
ኢዜማ ከዚህ አንጻር በሀገሪቱ ያለውን ጸጥታ በማስተካከልና መረጋጋትን በማምጣት ምርጫውን ማድረግ እደሚቻል ይገልጻል፡፡ ምርጫውን ለማድረግና የሀገርን ደህንነት ለማስቀጠል መንግስት የዕለት ከዕለት ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርቲው ጠይቋል፡፡
የፓርቲው ምክትል መሪ አቶ አንዱአለም አራጌ አሁን ባለው ሁኔታ በዚህ ዓመት ምርጫ ለማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው ያሉ ሲሆን ይህ ማለት ግን ምርጫ ለማድረግ ሁሉም ነገር ዝግ ነው ማለት አይደለም ብለዋል፡፡
በቅርቡ የጥምቀት በዓል አከባበር ወቅት በተወሰኑት አካባቢዎች በተለይም በአቦምሳ የከተራ በዓል አለመከበሩን እንዲሁም የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዳይከበር እንቅፋት የሆኑ አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡና ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ ፓርቲው ጠይቋል፡፡
ኢዜማ የምርጫ ወረዳዎችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንደዚሁም ሕዝባዊ ውይይቶች በሚያካሂድበት ወቅት እክል እየገየጠመኝ ነው ያለው ፓርቲው ወደምርጫ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት ሕዝቡ ሕገ-መንግሥታዊ የሆነውን የመሰብሰብ መብቱን መጠቀም የማይችልበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ብሏል፡፡
የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን መጠበቅና ሥርዓት አልበኝነትን በጋራ በቃ ማለት ይገባልም ብሏል ኢዜማ፡፡
ፓርቲው አሁን ላይ ከ400 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም በዛሬው መግለጫው አስታውቋል፡፡