58 ሰራተኞቹ እና አመራሮቹ በኦሮሚያ ክልል በእስር ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ገለጸ
በኦሮሚያ ክልል ያሉት ቅርንጫፎቹ የተዘጉበት ምርት ገበያ ለፌደራል መንግስት ቅሬታ ማቅረቡን ገለጸ
የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ "በምርት ገበያው ስለቀረቡ ጉዳዮች የማውቀው ጉዳይ የለም" ብሏል
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኦሮሚያ ክልል ያሉት ሰባት ቅርንጫፎቹ በኦሮሚያ ፖሊስ መዘጋታቸውን እና ሰራተኞቹ መታሰራቸውን ገልጿል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ግን ስለቅርንጫቹ መዘጋት እና ስለሰራተኞቹ መታሰር ጉዳይ አላውቅም ብሏል፡፡
ከ14 ዓመት በፊት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአገር አቀፍ ደረጃ 25 የግብርና ምርቶች ናሙና መቀበያ እና ምርት መቀበያዎች ማዕከሎች ያሉት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ሰባቱ በኦሮሚያ ክልል ይገኛሉ።
በምርት ገበያው የኮርፖሬት ኮሙንኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ነጻነት ተስፋዬ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት “በጊንቢ፣ አዳማ፣ ጅማ፣ በደሌ፣ ቡሌሆራ፣ ነቀምት እና መቱ ያሉ የምርት ገበያ ማዕከሎች ከሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ፖሊስ ታሽገዋል፡፡”
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ከሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ሰባቱን ማዕከላት እንዳሸጋቸው የገለጹት አቶ ነጻነት እስከአሁን ድረስ ፖሊስ ማዕከላቱን ለምን እንዳሸጋቸው እና ሰራተኞችን እንዳሰራቸው እንዳላሳወቃቸው ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
ለጉዳዩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ምርት ገበያው ጉዳዩን ለንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሳውቆ ከፌደራል መንግስት ተቋማት ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑንም አቶ ነጻነት አክለዋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ የምርት ገበያው መጋዝኖች ይሰሩ የነበሩ ሰራተኞችን በሙሉ አስሮ ነበር፣ አሁን ላይ የተወሰኑት ከእስር መለቀቃቸውን ሰምተናል የሚሉት አቶ ነጻነት ይሁንና “58 አመራሮች እና ሰራተኞች አሁንም በእስር ላይ ናቸው” ብለዋል፡፡
የምርት ገበያው መጋዝኖች መታሸግ እና ከስራ ውጪ መሆን አምራች አርሶ አደሮች፣ ምርት ላኪዎች ምርቶቻቸውን ለተቋሙ አቅርበው ወደ ውጪ እንዳይላክ በማድረጉ ሀገሪቱ ገቢ እንድታጣ እያደረገ መሆኑን ም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አስቀድመው ምርት ወደ መጋዝኖቹ የላኩ አርሶ አደሮች እና ምርት ላኪዎች ምርታቸው መጠኑ ሊቀንስ አልያም ሌላ ያልተገመቱ ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉም አቶ ነጻነት ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ይሄንን ለምን እንዳደረገ አናውቅም ያሉት ዳይሬክተሩ ድርጊቱን ለምርት ገበያው እስካሁን አላሳወቀምም ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል የራሱን ምርት ገበያ አቋቁሞ ቡና እና መሰል ምርቶችን ወደ ውጭ ሀገራት እየላከ ነው? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም ክልሉ የራሱን ምርት ገበያ አላቋቋመም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አሁን ላይ የውጪ ንግድን ለማበረታታት ሲባል በተለይም ቡናን ወደ ውጪ መላክ የሚችሉት የኢትዮጵያ ምርት ገበያውን ጨምሮ ህብረት ስራ ማህበራት እና ቡና ላኪ ኩባያዎች ቡናን ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ላይ መሆናቸውን ይህም በህግ እንደተፈቀደላቸው ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ምክትል ቢሮ ሀላፊ ኮለኔል አበበ ገረሱ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት በክልሉ የሚገኙ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ማዕከላት ለምን እንደታሸጉ እና ሰራተኞቹም ለምን እንደታሰሩ ላቀረብንላቸው ጥያቄ "በምርት ገበያው ስለቀረቡ ጉዳዮች የማውቀው ጉዳይ የለም" ሲሉ ምለሽ ሰጥተውናል፡፡