ትግርኛ ተናጋሪ የሰራዊት አባላትን ከሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የማስኮብለል ስራ መሰራቱን መከላከያ አስታወቀ
ከሰሞኑ በአቢዬ ተሰማርተው የነበሩ ከ500 በላይ የትግራይ ተወላጅ የሰራዊቱ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ አልፈቀዱም የሚሉ ዘገባዎች እንደነበሩ ይታወሳል
የተወሰኑ ወታደሮች ሰላም ለማስከበር በሄዱበት አገር መቅረታቸውንም መከላከያው ገልጿል
ሰላም ለማስከበር በውጭ ሃገራት የተሰማሩ ትግርኛ ተናጋሪ የሰራዊት አባላትን የማስኮብለል ስራ መሰራቱን መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ህወሓት በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ የሚገኙ ትግርኛ ተናጋሪዎችን "ኢንፍልትሬት" በማድረግና ለእኩይ አላማ በማዘጋጀት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሰሜን ዕዝን ማጥቃቱን ያስታወሰው ሚኒስቴሩ ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻው ሲጀመር ከወታደር እስከ ከፍተኛ አመራር ያሉ ትግርኛ ተናጋሪዎች "ለዘመቻው ስኬትና እርስ በእርስ እንዳንማታ ሲባል" ደመወዝና ቀለባቸው ሳይቋረጥ በቤታቸው እንዲቆዩ መደረጉን ገልጿል፡፡
ከሰሜን ዕዝ ጥቃት በፊት ወደ ውጭ ሀገር ሰላም ለማስከበር የተላኩ ትግርኛ ተናጋሪዎች ግን በሰራዊታችንና በተልዕኮው ላይ ችግር አይፈጥሩም በሚል በስራቸው እንዲቀጥሉ ተደርጎም ነበር እንደ ሚኒስቴሩ ገለጻ፡፡
ሆኖም ትግርኛ ተናጋሪ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አባላቱ ወደ ሀገራቸው እንዳይመለሱ "በውጭ በሚገኙ የህወሓት ቅጥረኞች የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በመነዛቱ" አባላቱ ለውዥንብር ተዳርገዋል።
ሃገር ቤት ከተመለሳችሁ ትታሰራላችሁ የሚል የውሸት ማስፈራሪያ በመነዛቱ የሠራዊት አባላቱን የማስኮብለል ስራ መሰራቱንም ነው የገለጸው፡፡
በዚህም ምክንያት የተወሰኑ ወታደሮች ሰላም ማስከበር በሄዱበት አገር ቀርተዋል፡፡
እንዲህ ዐይነቱ ሁኔታ ከአሁን ቀደምም በዳርፉር፣ ተልእኮ ላይ ተሰማርተው በነበሩ ጥቂት የሰራዊቱ አባላት ዘንድ አጋጥሞ ነበር፡፡ ሱዳን ከሚገኘው "ሳምሪ" ተቀላቅለው ሲዋጉ የሞቱም እንደነበሩም ገልጿል ሚኒስቴሩ፡፡
ሁሉንም ጫና ተቋቁመው ሃገርና ተቋማቸው የሰጣቸውን ግዳጅ ፈፅመው የተመለሱ ትግርኛ ተናጋሪ የሰራዊቱ አባላት መኖራቸውን በመጠቆምም አመስግኗል።
በህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻው ወቅት በቤታቸው እንዲቆዩ የተደረጉ እና ከሠላም ማስከበር የተመለሡ በሺዎች የሚቆጠሩ ትግርኛ ተናጋሪ የሠራዊት አባላት እና ሲቪል ሠራተኞች ዛሬም መብትና ጥቅማቸው እንደሚከበርና አሁን ያለው ግጭት በማናቸውም አግባብ ከተፈታ ወደ ሥራቸው ተመልሰው ሃገራቸውን ያገለግላሉ በሚል እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡
አሁንም በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ያሉትም ሆኑ ለጊዜው ከስራ ውጭ የሆኑ ወታደሮች "በወያኔ አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ሳትንበረከኩ አገራችሁን እንድታገለግሉ" ሲልም ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከሰሞኑ በሱዳን በአቢዬ ግዛት ተሰማርተው የነበሩ 528 ትግሬኛ ተናጋሪ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ተልዕኳቸውን ቢያጠናቅቁም ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ፍቃደኛ አይደሉም በሚል በተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘገብ ነበረ፡፡
የሰራዊት አባላቱ በሱዳን ፖለቲካዊ ጥገኝነት ስለመጠየቃቸውም ነበር ኤ.ኤፍ.ፒ የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ቃል አቀባይን ዋቢ አድርጎ የዘገበው፡፡
አል ዐይን አማርኛም በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስቴርን እና የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊዎችን አግኝቶ ስለ ዘገባው ለማጣራትና ምላሽ ለማግኘት ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ ሆኖም ጥረቱ አልተሳካም፡፡
በአቢዬ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት በሌላ እንዲተካ ሱዳን ደጋግማ ስትጠይቅ እንደነበር አል ዐይን አማርኛ ከአሁን ቀደም መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ጥያቄው በተመድ በኩል ተቀባይነት አግኝቶ በሱዳን በኩል የነበሩ የሰራዊቱ አባላት ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል፡፡
የሰላም ማስከበር ተልዕኮን የሚመለከተው የተመድ የስምምነት ህግ የትኛውም ወደ ሃገሩ ለመመለስ የማይፈልግ የተልዕኮ አባል ባለበት ጥገኝነት የመጠየቅ መብት እንዳለው ያትታል፡፡ ይህን ስምምነትም ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት ፈርመውታል፡፡
ትግርኛ ተናጋሪ የኢትዮጵያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ አባላት ይህኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሱዳን ለመቅረት መወሰናቸውንና የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቃቸውንም ነው በቅርቡ ከተልዕኮው የተመለሱና ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈለጉ የሰራዊቱ አባላት ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩት፡፡
በአብዬ ግዛት ያለው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል የሚወጣ ከሆነ ለከፈለው መስዋዕትነት ክብር ተሰጥቶት ሊሆን ይገባል-ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
በሱዳን በሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሰሩ የትግራይ ተወላጆች አባላቱን ያግባቡና ጅምላ ጭፍጨፋ እየተፈጸመ ነው በሚል ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ይቀሰቅሱ እንደነበርም ነው ተመላሽ አባላቱ የገለጹት፡፡ ይህ ከባለፈው ዓመት ወርሃ የካቲት ጀምሮ የሆነ ነው እንደ አባላቱ ገለጻ፡፡
በማይካድራ እና በአካባቢው ጅምላ ጭፍጨፋን ፈጽሞ ወደ ሱዳን እንደተሻገረ የሚነገርለትን ሳምሪ የወጣቶች ቡድን ትቀላቀላላችሁ በሚል ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ እንዳሉም ገልጸዋል፡፡ ሆኖም አል ዐይን ይህን በራሱ አላረጋገጠም፡፡