ዩ.ኤ.ኢ ሴቶችን ለማብቃት እስካሁን ከ322 ሚሊየን ዶላር በላይ አውጥታ እየሰራች መሆኑን አስታወቀች
“ሴቶችን ማብቃት እና ጥበቃ ማድረግ” በሚል ርዕስ ዩኤኢ እና ኢትዮጵያን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ዌቢናር ተካሂዷል
ሴቶችን ማብቃት ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ከኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የትብብር መስኮች አንዱ ነው
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ሴቶችን ለማብቃት እስካሁን ከ322 ሚሊየን ዶላር በላይ አውጥታ እየሰራች መሆኑን አስታወቀች።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የሀገሪቱ ኤምባሲ እና የኢትዮጵያ ሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር “ሴቶችን ማብቃት እና ጥበቃ ማድረግ” በሚል ርዕስ ያዘጋጁት ዌቢናር (የበይነ-መረብ ውይይት) በትናትናው እለት ተካሂዷል።
በአዲስ አበባ የዩኤኢ ኤምባሲ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ሚዲያ ጉዳዮች ኃላፊ ታላል አል አዚዚ በዌቢናር ባደረጉት ንግግር፣ ሴቶችን ማብቃት እና ጥበቃ ማድረግ በዩ.ኤ.ኢ የልማት እቅድ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
ሀገሪቱ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ቅድሚያ ከምትሰጣቸው ቁልፍ ተግባራት ውስጥ “ሴቶችን ማብቃት እና የሴቶች ጥበቃ” አንዱ መሆኑንም ተናገረዋል።
ዩኤኢ እስካሁን ሴቶችን ትኩረት በማድረግ ሰብአዊ እንቅስቃሴዎች እና ጣልቃ ገብነቶችን ለማስቆም ከ322 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጪ ማደረጓንም አስታውቀዋል።
ሴቶችን ማብቃት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ትብሮች ውስጥ አንዱ ነው ያሉት ታላል አል አዚዚ፤ በዚህም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር የሴቶች አቅም ግንባታ፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠናዎችን የማመቻቸት እንዲሁም በንግድ ስራ ላይ ያሉ ሴቶችን የመደገፍ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በዩ.ኤ.ኢ የሴቶች ህብረት የሴቶች ድጋፍ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር መርያም አል ማንደሃሪ በበኩላቸው፣ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶችን ለማብቃት በርካታ ስራዎችን ስትሰራ መቆቷን አንስተው፤ በፈረንጆች በ2019 በዩ.ኤ.ኢ እና በተባበሩት መንግስታት ትብብር በመካከለኛው ምስራቅ፣ በእሲያ እና በአፍሪካ ከ300 በላይ የሚሆኑ ሴቶች በጸጥታ እና ደህንነት ዘርፍ ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉንም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር የሴቶች ተሳፎ ዳይሬክተር ስለሺ ታደሰ በበኩላቸው፤ አዲሱ የኢትዮጵያ የ10 ዓመት የልማት እቅድ “ሴቶችን ማብቃት እና የሴቶች ጥበቃ” ላይ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።