ጥያቄው ተቀባይነትን የሚያገኝ ከሆነ ጉባዔው ህዳር 2023 ላይ በአቡ ዳቢ የሚካሄድ ይሆናል
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) እ.ኤ.አ የ2023ቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባዔን (Cop28) በአቡዳቢ ለማዘጋጀት ጥያቄ አቀረበች፡፡
ጥያቄው ተቀባይነትን የሚያገኝ ከሆነ 28ኛው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ህዳር 2023 ላይ በአቡ ዳቢ የሚካሄድ ይሆናል፡፡
ዩኤኢ ጥያቄውን ማቅረቧን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትሩ ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ ዛሬ አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ የአየር ንብረት ለውጥ ከባድ ተጽዕኖን ሊያሳርፍ ቢችልም የስራ ዕድል ሊፈጠርበት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ዩኤኢ ለኢነርጂ ዘርፍ አማራጮች ትኩረት መስጠቷንና በዘርፉ ብዙ ሃብት ፈሰስ ማድረጓን በመጠቆም ከአሁን ቀደም ያልታዩ በዘርፉ የመሰማራት ፍላጎቶች እንዳሉ ተመልክተናልም ብለዋል፡፡
ሼክ አብዱላህ ጉባዔው በዘርፉ ያለውን እድል ለመጠቀም የሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎችን ይፈጥራል ያሉም ሲሆን ከሃገራት ጋር ተባብረው እንደሚሰሩም ነው የገለጹት፡፡
የፕሬዝዳንት ባይደን ልዩ የአየር ንብረት መልዕክተኛ ጆን ኬሪ በቅርቡ ወደ አቡ ዳቢ አቅንተው በቀጣናዊ ቀጣይ የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎች ላይ መክረው ነበረ፡፡ ከምክክሩ በኋላ ዩኤኢ እና አሜሪካ በምግብ ዋስትና ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
የዘንድሮው Cop28 በስኮትላንድ ግላስኮው ነው የሚካሄደው፡፡ 30 ሺ ያህል ታዳሚዎች እንደሚኖሩትም ይጠበቃል፡፡
ዩኤኢ የዓለም አቃፍ ታዳሽ ኃይል ዓመታዊ ጉባዔ ቋሚ አዘጋጅ ነች፡፡ የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነትን ተቀብለው ከፈረሙ የቀጣናው ሃገራት መካከልም ቀዳሚዋ ነች፡፡ ግዙፍ የጸሃይ ኃይል አማራጮችን ከገነቡና በርካሽ ከሚያቀርቡ ሃገራት መካከልም ናት፡፡
ይህ Cop28ን ለማስተናገድ የሚያስችል ስራ እንዳላት የሚያሳይ ነው እንደ ሃገሪቱ ዜና አገልግሎት (ዋም) ዘገባ፡፡
ለታዳሽ ኃይል ግንባታዎች ትኩረት ሰጥታ የምትሰራው ዩኤኢ በ6 አህጉራት በሚገነቡ የታዳሽ ኃይል ልማት ፕሮጄክቶች ላይ 17 ቢሊዬን ዶላር ገደማ ገንዘብን ፈሰስ አድርጋለች፡፡
በተለያዩ አጋሮቿ በኩል በድጋፍና ብድር መልክ 1 ቢሊዬን ዶላር ፈሰስ ማድረጓንም የዋም ዘገባ ያመለክታል፡፡