ሶማሊላንድ በሀርጌሳ የሚገኘው የግብጽ ባህላዊ ቤተ መጽሃፍት በቋሚነት እንዲዘጋ አዘዘች
ራስ ገዟ ሶማሊላድ የቤተ መጽሃፍቱ ሰራተኞች በ72 ሰዓታት ውስጥ ሀርጌሳን እንዲለቁ አዛለች
ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረሙት የወደብ መግባቢያ ስምምነት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ተቀማጭነታቸውን በሀርጌሳ ላደረጉ ዲፕሎማቶች አስታውቃለች
ሶማሊላንድ በሀርጌሳ የሚገኘው የግብጽ ባህላዊ ቤተ መጽሃፍት በቋሚነት እንዲዘጋ አዘዘች፡፡
ራስ ገዟ ሶማሊላንድ በሀርጌሳ ያለው የግብጽ ባህላዊ ቤተ መጽሃፍት በቋሚነት እንዲዘጋ መወሰኗን ገልጻለች፡፡
የሶማሊላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤክስ አካውንቱ ለይ እንዳስታወቀው በሀርጌሳ ያለው የግብጽ ቤተ መጽሃፍት እንዲዘጋ የተወሰነ ሲሆን የቤተ መጽሀፍት ቤቱ ሰራተኞችም በ72 ሰዓት ውስጥ ሀርጌሳን ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል፡፡
እንደ ሚኒስቴሩ መግለጫ ሶማሊላንድ ይህንን እርምጃ የወሰደችው ከደህንነት ጋር በተያያዘ ነው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢሳ ክዛ ሞሀሙድ ተቀማጭነታቸው በሀርጌሳ ላደረጉ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች ስለ ሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ የወደብ ስምምነት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል ተብሏል፡፡
ሚኒስትሩ ለዲፕሎማቶቹ ከኢትዮጵያ ጋር ያደረጉት የወደብ መግባቢያ ስምምነት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን እና በቅርቡ የትግበራ ስምምነት እንደደረግ መናገራቸው ተገልጿል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም “የግብጽ ጦር በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ መግባቱ ያሳስበናል፣ የግብጽ ጦር በሶማሊላንድ መስፈሩ በአካባቢው ሀገራት የእጅ አዙር ጦርነት እንዲነሳ ምክንያት ይሆናል“ ማለታቸውም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ ስምምነት ካደረገች በኋላ ከሶማሊ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ሻክሯል፡፡
ቱርክ በሶማሊያ የሚሳኤል እና የጠፈር ሮኬት መሞከርያ ጣቢያ ልትገነባ ነው
ሶማሊያ ስምምነቱ ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው በሚል ጉዳዩን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት፣ አፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ የወሰደችው ሲሆን ተቋማቱ ሁለቱ ሀገራት አለመግባባታቸውን በውይይት እንዲፈቱ አሳስበዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ስምምነቱን ተከትሎ ሶማሊያ ከግብጽ እና ቱርክ ጋር ወታደራዊ ትብብሮችን ለማድረግ ስምምነት ያደረገች ኢትዮጵያ በበኩሏ ሞቃዲሾ ከግብጽ ጋር ያደረገችው ስምምነት እንደሚያሳስባት አስጠንቅቃለች፡፡
የኢትዮጵያ ጦር ሀይሎች አዛዥ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሰሞኑ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ከሆነችው ግብጽ ጋር ያልተገባ ስምምነት ማድረጓን እንድታቆም ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡