ግብጽ እና ሶማሊያ የጋራ ወታደራዊ ስምምነቶችንም በካይሮ ተፈራርመዋል
ግብጽ በሶማሊያ ኢምባሲዋን ከፈተች፡፡
ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር የወደብ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ግብጽ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ወዳጅነት እያጠናከረች መጥታለች፡፡
ይህን ተከትሎም ግብጽ በሞቃዲሾ ኢምባሲዋን የከፈተች ሲሆን የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማን ይዞ የሚበረው የግብጽ አየር መንገድም ከካይሮ ሞቃዲሾ የቀጥታ በረራ ጀምሯል፡፡
ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ጋር አለመግባባት ውስጥ ያለችው ግብጽ የሶማሊያ ሉዓላዊ እና ደህንነት እንዳይሸራረፍ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች፡፡
ይህ በዚህ እንዳለም የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ በካይሮ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከግብጹ አቻቸው አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን ወታደራዊ ትብብሮችን ማድረግ የሚያስችሉ የሁለትዮሽ ስምምነቶችንም ተፈራርመዋል፡፡
የሁለትዮሽ ወታደራዊ ስምምነት የሀገራቱ መከላከያ ሚኒስትሮች የተፈራረሙ ሲሆን የስምምነቶቹ ዝርዝር ይዘት እስካሁን ይፋ አልተደረገም፡፡
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በሶማሊላንድ የወደብ ስምምነት እና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ያለባቸውን አለመግባባት ለመፍታት በቱርክ አደራዳሪነት በአንካራ የተደረጉ ቀጥተኛ ያልሆኑ ድርድሮች ያለውጤት መጠናቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ሀገራቱ በመስከረም ወር ላይ ሶስተኛ ዙር ድርድራቸውን በአንካራ እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡