ኢትዮጵያ በጸጥታው ምክር ቤት በግብጽ ለቀረበባት ክስ ምላሽ ሰጠች
ግብጽ አዋጭነታቸው ያልተረጋገጡ ፕሮጀክቶችን በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች መሆኗን ኢትዮጵያ ገልጻለች
ግብጽ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ በጸጥታው ምክር ቤት ዘጠኝ ጊዜ ክስ መስርታለች
ኢትዮጵያ በጸጥታው ምክር ቤት በግብጽ ለቀረበባት ክስ ምላሽ ሰጠች፡፡
ከአንድ ሳምንት በፊት ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ አምስተኛው ዙር ውሃ ሙሌት ማከናወኗ እና ተጨማሪ ተርባይኖች ሀይል ማመንጨት መጀመራቸውን ይፋ ማድረጓ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም ግብጽ ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ የተናጠል እርምጃ ወስዳለች በሚል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ክስ አስገብታለች፡፡
በግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተፈረመው ይህ ደብዳቤ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2015 የተፈረመውን የመርህ ስምምነት ጥሳለች፣ ድርጊቱም ለአካባቢው ሀገራት አለመረጋጋት የሚሆን ነው፣ ግብጽ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በተመድ ቻርተር አማካኝነት እርምጃ ትወስዳለች ሲልም ያትታል፡፡
ኢትዮጵያ በግብጽ ለቀረበባት ክስ በይፋ ባሳለፍነው ቅዳሜ ለተመድ ይፋዊ ምላሽ መስጠቷን አል ዐይን ከታማኝ ምንጮች አረጋግጧል፡፡
አል ዐይን የተመለከተው ይህ ደብዳቤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀስላሴ የተፈረመ ሲሆን ደብዳቤው ለወቅቱ የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ስሎቬኒያ የተጻፈ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለግብጽ ምላሽ በሰጠችበት በዚህ ደብዳቤ ላይ እንደገለጸችው የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና ሱዳን ሀገራት የሶስትዮሽ የባለሙያዎች ቡድን ባስቀመጠው እና በተስማሙት መርህ መሰረት የግድቡን ውሃ ሙሌት እያከናወነች መሆኗን ገልጻለች፡፡
የሶስትዮሽ ሀገራት ባለሙያዎች ቡድን ከዚህ በፊት በተስማሙት መሰረት የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ የከፋ ጉዳት በማያደርስ መልኩ የሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት እየተካሄደ መሆኑን ኢትዮጵያ አስታውቃለች፡፡
ከግድቡ ውሃ አሞላል ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለሱዳን እያጋራች መሆኗን የገለጸችው ኢትዮጵያ በአንጻሩ ግብጽ አዋጭነታቸው ያልተረጋገጡ ፕሮጀክቶችን የወንዙን ተፋሰስ ሀገራት ሳታሳውቅ እና ሳታማክር ስትገነባ መቆየቷንም ጠቅሷል፡፡
በአጠቃላይ ግብጽ ከፈረንጆቹ 2020 ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን በጸጥታው ምክር ቤት ዘጠኝ ጊዜ ክስ እንደመሰረተች የገለጸው ይህ ደብዳቤ ኢትዮጵያ ሁልጊዜ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች፡፡
ግብጽ የሶስትዮሽ ውይይቶችን በተደጋጋሚ እንዳቋረጠች፣ በቅኝ ግዛት ዘመን የነበሩ ስምምነቶች አሁንም እንዲከበሩ መፈለግ እና ታሪካዊ የውሃ ድርሻችን ይከበር የሚሉ አስተያየቶች ላይ ከመቆሟ ባለፈ ጉዳዩን በድርድር የመፍታት ፍላጎት እንደሌላትም ኢትዮጵያ ለጸጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ላይ ጠቅሳለች፡፡
ግብጽ ዓለም አቀፍ ህጎችን መሰረት በማድረግ ልዩነቶችን ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ኢትዮጵያ የራሷን ተፈጥሯዊ ሀብት መጠቀም እንዳትችል የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ መቆየቷም በደብዳቤው ላይ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ አሁንም በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶችን ለመፍታት ከግብጽ እና ሱዳን ጋር በናይል ወንዝ ትብብር ማዕቀፍ አልያም በአፍሪካ ህብረት ስር ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን አሳውቃለች፡፡