የአውሮፓ ህብረት በኮሮና ቫይረስ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተጎዳውን የግብጽን ኢኮኖሚ መደገፍ እንደሚፈልግ አስታውቋል
ግብጽ ከአውሮፓ ህብረት ጋር የ42 ቢሊዮን ዶላር ንግድ ስምምነት ተፈራረመች፡፡
የግብጽ- አውሮፓ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ጉባኤ በካይሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ኩባንያዎች በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ የሁለትዮሽ ንግድ ስምምነቶች መፈረማቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮንደር ሊን እንዳሉት የግብጽ እና አውሮፓ ህብረት የ42 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ንግድ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ በቀጣዮቹ ቀናት ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ይደረጋሉ የተባለ ሲሆን የግብጽ መረጋጋት ለአውሮፓ መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንቷ አክለውም የግብጽ ኢኮኖሚ በኮሮና ቫይረስ፣ በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ምክንያት መጎዳቱን ተናግረው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት የአውሮፓ ህብረት ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል ተብሏል፡፡
ከተደረጉ የንግድ እና ኢንቨስትመንቶች መካከልም በሀይድሮጅን ልማት፣ ውሃ አስተዳድር፣ ኬሚካል፣ ትራንስፖርት እና አቪዬሽን ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
የአውሮፓ ህብረት ለግብጽ የ7 ነጥብ 4 ቢሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገ
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ በበኩላቸው ሀገራቸው ለአውሮፓ ኩባንያዎች ተስማሚ እና አትራፊ የሆኑ የኢንቨስትመንት ስራዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ እና በሌሎች ሀገራት ያሉ ዓለም አቀፍ ቀውሶችን ለመፍታት ግብጽ እና የአውሮፓ ህብረት የበለጠ መተባበር እንዳለባቸውም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል፡፡
የግብጽ ኢኮኖሚ በእስራኤል-ሐማስ ጦርነት ምክንያት እየተጎዳ ነው የተባለ ሲሆን ህገወጥ ስደተኞች ወደ አውሮፓ እንዳይጓዙ ከአውሮፓ ህብረት የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡