የአውሮፓ ህብረት ለግብጽ የ7 ነጥብ 4 ቢሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገ
የድጋፍ ስምምነቱን የህብረቱ ኮሚሽነር ኡርሱላ ቮንደርሌን እና የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በካይሮ ተፈራርመዋል
ግብጽ ከህብረቱ ያገኘችው ድጋፍ ያጋጠማትን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመሻገር ያግዛታል ተብሏል
የአውሮፓ ህብረት ለግብጽ የ7 ነጥብ 4 ቢሊየን ዩሮ (8 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር) ድጋፍ አደረገ።
የድጋፍ ስምምነቱን የህብረቱ ኮሚሽነር ኡርሱላ ቮንደርላይን እና የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ትናንት በካይሮ ተፈራርመዋል።
ህብረቱ ከግብጽ ጋር በንግድ፣ በኢነርጂ፣ በደህንነት እና ሌሎች ዘርፎች ግንኙነቱን ለማጠናከር ልኡኩን ልኮ መክሯል።
በካይሮ የተፈረውመው የድጋፍ ስምምነትም ካይሮ ከህብረቱ 5 ቢሊየን ዩሮ በረጅም ጊዜ እና በአነስተኛ ወለድ የሚከፈል ብድር እንድታገኝ ያስቻለ መሆኑን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
ለተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች የሚውል 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ዩሮ ድጋፍ መደረጉም ነው የተጠቀሰው።
ህብረቱ ግብጽ በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ ሀገራት የሚደረግ ህገወጥ ስደትን ለመከላከል ለምታደርገው ትብብር 200 ሚሊየን ዶላር ለመስጠትም ቃል ገብቷል።
ከህብረቱ ኮሚሽን ኡርሱላ ቮንደርሌን ጋር ወደ ካይሮ ያመሩት የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂና ሜሎኒ፥ የተፈረመው ስምምነት “ህገወጥ የሰደተኞች ጎርፍን ለመግታት ውሳኝ ነው” ብለዋል።
ባለፉት ወራት በሊቢያ በኩል አድርገው ወደ ግሪክ ደሴቶች የሚገቡ የግብጽ፣ ባንግላዲሽ እና ፓኪስታን ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የጠቀሱት የግሪክ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪሪያኮስ ሚትሶታኪስ፥ “አዳዲስ የስደተኞች የጉዞ መስመሮች እንዳይከፈቱ ከግብጽ ጋር በትብብር እንሰራለን” ነው ያሉት።
የጋዛው ጦርነት ቀጠናዊ ተሰሚነቷን ይበልጥ ከፍ ያደረገላት ግብጽ ባለፉት ወራት ከአለማቀፍ የብድር ተቋማት እና ከተለያዩ ሀገራት የ20 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ቃል እንደተገባላት ገልጻለች።
ካይሮ የአለማቀፉን የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) የገንዘብ የመግዛት አቅም አዳክሚ ጥያቄ መቀበሏም ኢኮኖሚዋን ለማረጋጋት እና የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር የሚያግዝ ድጋፍ እንድታገኝ አድርጓታል።