የግብጽ የደህንነት ኃላፊ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከሱዳን መሪ ጋር መከሩ
የስለላ ኃላፊው ሜጀር ጀነራል ካሜል የሁለትዮሽ ግንኙነትን መደገፍና ማጎልበት በተመለከተም ተወያይተዋል
በህዳሴው ግድብ ላይ ግብጽና ሱዳን ብሄራዊ ደህንነት በሚመለከት ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል
የሱዳን ሉዓላዊነት ምክር ቤት ኃላፊ ሌተናል ጀነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን በፕሬዝዳንታዊ ቤተ-መንግስት የግብጽ የመረጃና ደህንነት ኃላፊ ሜጀር ጀነራል አባስ አነጋግረዋል።
የግብጽ የስለላ ኃላፊ ሜጀር ጀነራል ካሜል ከሌ/ጄነራል አልቡርሃን ጋር ባደረጉት ቆይታ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ የሁለትዮሽ ግንኙነትን መደገፍና ማጎልበት በተመለከተ ተወያይተዋል ነው የተባለው።
ኃላፊው የሁለቱን ሀገራት የጋራ ትብብር በተመለከተ ከፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ባለፈው ወር ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኤል ሲሲና የሱዳን የሽግግር ሉዓላዊ ም/ቤት መሪን በሪያድ ከአረብ-ቻይና የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን መወያየታቸው ይታወሳል።
በህዳሴው ግድብ ግንባታ ሂደት ላይም ሁለቱ መሪዎች ሀሳባቸውን በመለዋወጥ “የውሃ ጉዳይ የግብጽ እና የሱዳን ህዝቦች የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ” ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ከስምምነት ላይ ደርሰዋልም ነው የተባለው።
ከዓመት በፊት የሦስትዮሽ ድርድሩ የቆመ ሲሆን፤ ግብጽና ሱዳን ከግድቡ ሙሌት በፊት ስምምነት መደረስን ቢወተውቱም ኢትዮጵያ ግን ውድ አድርጋዋለች።
ከውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨውና በአፍሪካ ትልቁ ፕሮጀክት ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ በ2003 ዓ.ም. ግንባታውን ጀምራለች።
የግድቡን ግንባታ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ቀጣናዊ ውዝግብ የተነሳ ሲሆን፤ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ግብጸና ሱዳን ጫና ለማሳደር በርካታ እርምጃዎችን ወስደዋልም። ሀገራቱ የውሃ ደህንነታቸውን ሲገልጹ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የልማት መብቷን በመጥቀስ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ያለውን ጠቀሜታ አበክሯ ገልጻለች።
ኢትዮጵያ በሁለት ተርባይኖች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የተከናወኑት ስራዎች በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ እጥረት እንደማይፈጠርም አረጋግጣለች።
በሪያዱ ውይይቱ ወቅት አልሲሲ በግብጽ የሱዳንን ደህንነት እና መረጋጋት ለመጠበቅ ያላትን አቋም እና ሱዳንን በቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃ ለመደገፍ ያላትን ጽኑ አቋም አስምረዋል ተብሏል።