የህዳሴው ግድብ ድርድር ዳግም ወደ ዋሽንግተን እንዲዛወር ተሞክሮ እንደነበር ተገለጸ
ኢትዮጵያ አንዱን ጫና ስትገላገል ተጨማሪ አጀንዳዎች እየመጡ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ተናገሩ
ኢትዮጵያን በተለያዩ ሀገራት ወክለው እየሰሩ ያሉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ወደ አዲስ አበባ ተጠርተዋል
የህዳሴው ግድብ ድርድርን ዳግም ወደ ዋሽንግተን እንዲዛወር ተሞክሮ እንደነበር ተገለጸ።
ኢትዮጵያን በተለያዩ ሀገራት ወክለው እየሰሩ ያሉ አምባሳደሮች፣ ምክትል ሚሲዮን ሙሪዎች እና ሌሎች ዲፕሎማቶት ወደ አዲስ አበባ ተጠርተዋል።
ዲፕሎማቶቹ ወደ አዲስ አበባ የተጠሩት የእስካሁኑን ስራዎች ለመገምገም እና በቀጣይ የዲፕሎማሲ ዙሪያ ለመወያየት እንደሆነ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ገልጿል።
- ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ህጋዊ ስምምነት ላይ እንድትደርስ ጥሪ አቀረቡ
- 11 የግንባታ ዓመታት - ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና ውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ደመቀ መኮንን ለነዚህ ዲፕሎማቶች ባደረጉት ንግግራቸው ኢትዮጵያ አንዱን ፈተና ጨረስኩ ስትል ሌላ ወቅታዊ የዲፕሎማሲ ፈተና ይገጥማታል ብለዋል።
ላለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ በኒዮርክ፣ ብራስልስ እና ሌሎች የዲፕሎማሲ ማዕከላት ብርቱ ፈተና ገጥሞን ነበር የሚሉት ሚንስትሩ ጫናውን በብዙ መንገድ መክተን አሁን ላለንበት የእፎይታ ጊዜ ደርሰናል ሲሉ በንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል።
የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት፣ የህዳሴ ግድብ እና ሌሎች አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች እንደነበሩ የተናገሩት አቶ ደመቀ ኢትዮፕያውያን፣ ዲፕሎማቶቻችን እና በወዳጅ ሀገራት ጥረት የታሰበልንን ፈተና አልፈናልም ብለዋል።
አቶ ደመቀ አክለውም አፍሪካ ህብረት የመጨረሻ የዲፕሎማሲ ትግል ሜዳችን ዩሆነውን እንድንለቅ ብዙ ጫና ደርሶብናል ይሁንና ችግሮቻችንን ለመፍታት የግድ በዚህ ሜዳ እንዲዘልቅ መደረጉን ተናግረዋል።
"ከሰሞኑ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ወደ ዋሸንግተን እንዲመለስ ጫና ተደርጎ ነበር" ያሉት አቶ ደመቀ "ግድቡ ጥቁርነቱን እንዳይለቅ ማድረግ ችለናል"ም ብለዋል።
ይሁንና ሚንስትሩ አቶ ደመቀ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር በዋሸንግተን እንዲቀጥል ጫና ያደረሰውን አካል ከመናገር ተቆጥበዋል።
የተኩስ አቁም አድርጉ፣የሰብዓዊ ድጋፍ ያለገደብ ይግባ እና ተጠያቂነትን አስፍኑ የሚሉ አጀንዳዎች በኢትዮጵያ ላይ በሰፊው ጫና ሲደረግባቸው የነበሩ አጀንዳዎች ናቸው የሚሉት ሚንስትሩ የፌደራል መንግስት በሰፊው እየፈጸማቸው እንደሆነም በንግግራቸው ላይ አንስተዋል።