ኢትዮጵያ ከግድቡ ሙሌት በፊት ሱዳንና ግብፅ ለመረጃ ልውውጥ ባለሙያዎችን እንዲመድቡ ጋበዘች
የህዳሴ ግድበ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በመጭው ሐምሌ እና ነሃሴ ወር ላይ ይከናወናል
ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን መረጃ የሚለዋወጡ ሰዎቸ ስብሰባ ለማካሄድ ፍላጎት እንዳላት ሚኒስትሩ ገልጸዋል
ኢትጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድበ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በፊት ሱዳንና ግብፅ ለመረጃ ልውውጥ የሚሆኗቸውን ባለሙያዎች እንዲመድቡ ግብዣ አቀረበች።
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ኢትዮጵያ በመጪው የክረምት ወቅት ለምታከናውነው የውሃ ሙሌት ሀገራቱ የግድብ ባለሙያዎችን ኢንዲመድቡ በይፋ መጋበዛቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ለሱዳን የውሃ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ለግብፅ ውሃ ሚኒስቴር በላከው ደብዳቤ ነው ሁለቱ ሀገራት የፊታችን ሐምሌ እና ነሃሴ ወር ላይ የሚከናወነውን የውሃ ሙሌት በተመለከተ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል ባለሙያ እንዲመድቡ የጋበዘው።
በሚኒስትሩ ደብዳቤ መሠረት ግብዣው የሶስቱ ሀገራት ብሄራዊ ገለልተኛ የሳይንስ ምርምር ቡድን (NISRG) ባቀረበው የሙሌት የጊዜ ሰሌዳ ላይ በተደረሰው መግባባት ላይ በመመርኮዝ የቀረበ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ሙሌቱ በሐምሌ እና ነሐሴ ወር ውስጥ እንደሚከናወን፤ በወቅቱ በሚኖር የውሃ መጠን ላይ በመመርኮዝ እስከ መስከረም ወር ሊራዘም እንደሚችልም ተመላክቷል።
የግድቡ ግንባታ የደረሰበትን ሁኔታና የዝናብ ወቅት መድረሱን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ተግባራዊና አስፈላጊ የሆነ የንግግር መድረክ ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
መረጃ የሚለዋወጥ ሰው መመደብ ትክክለኛ የሆነ የመረጃ ልውውጥ ያፋጥናል፤ በአፍሪካ ህብረት ስር የሚደረገው የግድቡ ድርድር እስከሚጠናቀቅ ድረስ በሶስቱ ሀገራት መካከል መተማማን ይፈጥራል ብሏል መግለጫው፡፡
መግልጫው እንደጠቀሰው ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ በሱዳን ካርቱም በፈረንጆቹ 2015 በሶስቱ ሀገራት በተፈረመው “የመርሆች ስምምነት መሰረት” በመጀመሪያው የግድቡ ሙሌት ህጎችና መመሪያዎች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን መረጃ የሚለዋወጡ ሰዎቸ ስብሰባ ለማካሄድ ፍላጎት አላት ብለዋል፡፡