"በሱዳን መንግስት ወታደራዊ ክንፍ እየተነፋ ያለው የግጭት ጥሩምባ... የ 3ኛ ወገን ፍላጎቶችን ብቻ የሚያገለግል ነው" ውጭ ጉ/ሚኒስቴር
ሱዳን ኢትዮጵያ እንደወረረቻት ከገለጸች ከቀናት በኋላ ባወጣው መግለጫ የሱዳን መንግሥት ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ሚኒስቴሩ አሳስቧል
ሱዳን ኢትዮጵያን እንደወራሪ በመወንጀል የተሳሳተ የመረጃ ዘመቻ እያካሄደች እንደሆነና ትንኮሳዋን መቀጠሏን ሚኒስቴሩ ገልጿል
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ጉዳይ በተመለከተ የሱዳን መንግስትን ውጥረት የማባባስ እና ተንኳሽ ባህሪ አጥብቆ እንደሚያወግዝ አስታወቀ፡፡ ሚኒስቴሩ ዛሬ የካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚነሳ ማንኛውም ግጭት ከፍተኛ የሆነ ጉዳትን የሚያስከትል እና የሁለቱንም ሀገራት ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብላ እንደምታምን ገልጿል፡፡ ስለሆነም "በሱዳን መንግስት ወታደራዊ ክንፍ እየተነፋ ያለው የግጭት ጥሩምባ የሱዳንን ህዝብ በመጉዳት የሶስተኛ ወገን ፍላጎቶችን ብቻ የሚያገለግል እንደሚሆን የኢትዮጵያ መንግስት በፅኑ ያምናል" ይላል መግለጫው፡፡
ሁለቱ መንግስታት ማናቸውንም የድንበር ይገባኛል ወይም ማንኛውንም የግዛት ጥያቄዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል በቂ አሰራሮች እንዳሏቸው ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል፡፡ ሆኖም የሱዳን ብሔራዊ ጦር እ.ኤ.አ. በህዳር 2020 መጀመሪያ ላይ በማያወላውል ሁኔታ ኢትዮጵያን በመውረር የዓለም አቀፍ ህግ መሰረታዊ መርሆችን እና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚቻልበትን መንገድ ጥሷል ነው ያለው፡፡ ሱዳን ይህን በማድረጓ፣ የሁለቱም ሀገራት ዜጎች በሁለቱ መንግስታት በጋራ ከተመዘገቡት እርሻዎቻቸው እንዳይፈናቀሉ እንዲሁም ጉዳዩ በስምምነት እስኪፈታ ድረስ ነባራዊው ሁኔታ ባለበት እንዲቆይ የሚደነግገውን የሁለቱን የድንበር ስምምነቶች እንደጣሰችም ሚኒስቴሩ አንስቷል።
የጋራ ድንበሩን እንደገና የማካለል ሥራን ለማጠናቀቅ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩትን የጋራ የድንበር ኮሚቴዎች ጥረትም የሱዳን ወገን ዋጋ እንዳሳጣ ገልጿል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አክሎም "በሁለቱ ወንድማማች ሀገሮቻችን መካከል ካለው የወዳጅነት እና የትብብር መንፈስ በተቃራኒ የሱዳን ጦር ንብረቶችን ዘርፏል ፤ ካምፖችን አቃጥሏል ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በማጥቃት እና ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል ፤ የተለቀቁትን የኢትዮጵያ ወታደራዊ ካምፖች ተቆጣጥሯል" ብሏል፡፡
በመግለጫው እንደተጠቀሰው "በጣም የሚያሳዝነው ነገር በመሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን በተሳሳተ መንገድ በማቅረብ ሱዳን ሆን ብላ ተጠቂ የሆነችውን ኢትዮጵያን እንደወራሪ በመወንጀል ፣ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የራሷን ጥፋተኛነት እና ጠብ አጫሪነት የኢትዮጵያ በማስመሰል ሆን ብላ በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተ የመረጃ ዘመቻ እያካሄደች ነው፡፡" ተጨማሪ መሬቶችን ለመቆጣጠር ትንኮሳዋን ቀጥላለችም ነው ያለው፡፡
"በእነዚህ ሁሉ የሱዳን ጠብ የሚያባብሱ እና ቀስቃሽ ባህሪዎች መካከል ኢትዮጵያ ብዙ ትዕግስትን አሳይታለች ፤ ራስን የመከላከል ሕጋዊ መብቷን ከመጠቀም ከመቆጠቧም ባለፈ የድንበር ልዩነቶችን በሁለትዮሽ ስምምነቶች እና የጋራ የድንበር አሠራሮች መሠረት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኝነቷን ገልፃለች" ብሏል ሚኒስቴሩ። እናም ሰላማዊ መፍትሄ ላይ ለመድረስ የሚያስፈልገው የሁለቱ መንግስታት የፖለቲካ ፍላጎት እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
የሁለቱ ሀገራት መንግስታት ተፈጥሮ ምንም ይሁን ምን ፣ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦች የቆየ ወንድማዊ ግንኙነት እንዳላቸው ኢትዮጵያ በጽኑ እንደምታምንም ተገልጿል፡፡ ሚኒስቴሩ በመግለጫው እንዳለው ፣ የኢትዮጵያና የሱዳን ወዳጅ ሕዝቦችን ወደ አላስፈላጊ ጦርነት ለመግፋት "በሱዳን ጦር እየተደረገ ያለው ሙከራ በተለይ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ፣ ባጠቃላይ ደግሞ የቀጣናውን ሰላም ፣ መረጋጋትና ልማት የሚያደፈርስ ከባድ ስህተት ነው"፡፡
የድንበሩ ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ ቁርጠኝነቷን አረጋግጣ ባለችበት ወቅት የሱዳን መንግሥት ጠብ አጫሪ ድርጊቱን እንዲያቆም ፣ ከትንኮሳ በመቆጠብ ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ በድጋሚ ጥሪዋን አቅርባለች፡፡
የሱዳን መንግስት የሶስተኛ ወገን ፍላጎት አገልጋይ እንዳይሆን የሀገሪቱ ህዝብ እንዲከታተለው ፣ በተጨማሪም የድንበር ጉዳዮችን በሰላማዊ መንገድ ለማጠናቀቅ የአፍሪካ ሀገራት የሱዳን መንግስትን እንዲመክሩ ኢትዮጵያ ትጠይቃለች፡፡
ሚኒስቴሩ መግለጫውን ሲያጠቃልል ፣ የኢትዮጵያ መንግስት "ከፍተኛ ትዕግስት እና ጥልቅ ግንዛቤን ላሳየው" የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋናውን ያቀርባልም ብሏል፡፡
የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ዕሁድ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ የሱዳንን ድንበር ጥሳ ወረራ እንደፈጸመች ገልጿል። በዚህም ሳቢያ ለሚፈጠረው ማንኛውም ቀውስ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱን እንደምትወስድ ያስታወቀው ሚኒስቴሩ ወረራው መቼና በየት በኩል እንደተፈጸመ እንዲሁም ምን ጉዳት እንዳስከተለ ያለው ነገር የለም።