![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/11/273-110337-egypt-us-fm_700x400.jpg)
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ካይሮ ከጋዛ የሚወጡ ፍልስጤማውያንን እንድትቀበል ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል
ግብጽ የአረብ ሀገራት የትራምፕን የጋዛ እቅድ ውድቅ ማድረጋቸውን አስታወቀች።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ከአሜሪካ አቻቸው ማርኮ ሩቢዮ ጋር በዋሽንግተን መክረዋል።
በዚህ ምክክርም የአረብ ሀገራት የትራምፕን ጋዛን የመቆጣጠር እቅድ አጥብቀው ማውገዛቸውን ነው አብደላቲ ለሩቢዮ የነገሯቸው።
ሚኒስትሩ ፍልስጤማውያን ሳይፈናቀሉ ጋዛን መልሶ መገንባት እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ያሳያል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ሚኒስትሮቹ በትራምፕ የጋዛ እቅድ ዙሪያ ስለመምከራቸው ባይጠቅስም ሩቢዮ ሃማስ ከጦርነቱ በኋላ ዳግም ጋዛን ማስተዳደር እና የእስራኤል የደህንነት ስጋት መሆን እንደሌለበት መግለጻቸውን ጠቁሟል።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከአዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ጋር "በቀጠናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን" በትብብር እንደሚሰሩ መናገራቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
አብደላቲ በዋሽንግተን ከአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር ሲመክሩም የትራምፕን የጋዛ እቅድ መቃወማቸው ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከ17 ቀናት በፊት ፍልስጤማውያንን አስወጥቶ ጋዛን የመቆጣጠር እቅዳቸውን ይፋ ሲያደርጉ ግብጽ እና ዮርዳኖስ ፍልስጤማውያንን እንዲቀበሉ መጠየቃቸው ይታወሳል።
አወዛጋቢው እቅድ አስቀድሞ ፍልስጤማውያን ከጋዛ የሚወጡት በጊዜያዊነት እንደነበር ቢጠቅስም በሂደት የተሰጡት ማብራሪያዎች በቋሚነት እንደሚያፈናቅላቸው አመክተዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት እና የመብት ተሟጋቾች የትራምፕ የጋዛ እቅድ "የዘር ማጥፋት" ነው እያሉ ቢቃወሙትም ትራምፕ እቅዳቸውን ገፍተውበታል።
በእቅዳቸው ዙሪያ ፍልስጤማውያንን እንዲቀበሉ ከተመረጡ ሀገራት አንዷ ከሆነችው ዮርዳኖስ ንጉስ አብዱላህ ጋር ለመምከር ቀጠሮ መያዛቸውም ነው የተነገረው።
ሃማስ እስራኤል የጋዛውን የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሳለች በሚል ቅዳሜ ሊለቃቸው የነበሩ ታጋቾችን ለጊዜው እንደማይለቅ ማሳወቁን ተከትሎም ውጥረት የሚፈጥር አስተያየት ሰጥተዋል።
"ሁሉም ታጋቾች ቅዳሜ ቀትር ላይ መለቀቅ አለባቸው" ያሉት ትራምፕ፥ ሁሉም ታጋቾች የፊታችን ቅዳሜ ካልተለቀቁ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሊሰረዝ ይገባል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በአሜሪካ፣ ኳታርና ግብጽ አደራዳሪነት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ሃማስ በሰባት ዙሮች 33 ታጋቾችን ለመልቀቅ ተስማምቶ፤ በአምስት ዙሮች 21 ታጋቾችን ለቋል። ስምንቱ ታጋቾች ህይወታቸው ማለፉ መገለጹን ተከትሎ ቀሪ ሰባት ታጋቾች የፊታችን ቅዳሜ እና በቀጣዩ ሳምንት ይለቃቀሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
የትራምፕ የጋዛ እቅድ ግን የተኩስ አቁም ስምምነቱንና የታጋቾችና እስረኖች ልውውጡን አደናቅፎ ዳግም ጦርነት እንዲቀሰቀስ ሊያደርግ ይችላል የሚል ከፍ ያለ ስጋት ፈጥሯል።