ሀማስ እስከቀጣዩ ቅዳሜ ድረስ ሁሉንም ታጋቾች ካልለቀቀ ስምምነቱ ይፈርሳል ሲሉ ትራምፕ አስጠነቀቁ
ትራምፕ ግብጽና ጆርዳን ከጋዛ የሚፈለናቀሉትን ፍልስጤማውያን የማይቀበሉ ከሆነ የሚያደርጉላቸውን እርዳታ እንደሚያቆሙ ገልጸዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/11/243-104158-images-4-_700x400.jpeg)
ትራምፕ በሀማስ የተለቀቁት ታጋቾች ያሉበት ሁኔታና ቡድኑ ተጨማሪ ታጋቾች መልቀቅ እንደሚያቆም ማስታወቁ ስጋት ፈጥሮባቸዋል
ሀማስ እስከቀጣዩ ቅዳሜ ድረስ ሁሉንም ታጋቾች ካልለቀቀ ስምምነቱ ይፈርሳል ሲሉ ትራምፕ አስጠነቀቁ።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሀማስ ሁሉንም የእስራኤል ታጋቾች እስከ ቀጣዩ ቅዳሜ እኩለ ቀን ድረስ ካልለቀቀ የእስራኤል-ሀማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ተሰርዞ ግጭቱ ይቀሰቀሳል ብለዋል።
እስራኤል በጉዳዩ ላይ ብቻዋን ወሳኔ እንዳታሳልፍ የሰጉት ትራምፕ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ሊነጋገሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
ትራምፕ በኦቫል ኦፊስ በሰጡት መግለጫ በሀማስ የተለቀቁት ታጋቾች ያሉበት ሁኔታና ቡድኑ ተጨማሪ ታጋቾች መልቀቅ እንደሚያቆም ማስታወቁ ስጋት ፈጥሮባቸዋል። "እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ሁሉም ታጋቾች እስከ ቅዳሜ እኩለ ቀን ድረስ ካልተለቀቁ እኔ የምለው ሰርዙትና ድብልቅልቁ ይወጣ ነው። ታጋቾቹ ቅዳሜ እኩለ ቀን(12:00) ሰአት መለቀቅ አለባቸው" ብለዋል ትራምፕ።
ትራምፕ ታጋቾች በትንንሽ ቡድን ሳይሆን ሁሉም በጅምላ እንዲለቀቁ ይፈልጋሉ።
ትራምፕ ግብጽና ጆርዳን ከጋዛ የሚፈለናቀሉትን ፍልስጤማውያን የማይቀበሉ ከሆነ የሚያደርጉላቸውን እርዳታ እንደሚያቆሙ ገልጸዋል። ትራምፕ ከጆርዳኑ ንጉስ አብዱላህ ጋር በዛሬው እለት ይገናኛሉ ተብሏል።
ትራምፕ አሜሪካን ጋዛን የራሷ በማድረስ ማልማት እንደምትፈልግ ሲገልጹ የነበረውን ሀሳባቸውን ሰኞም ደግመውታል።
ግብጽና ጆርዳንን ጨምሮ በርካታ የአረብ ሀገራት ትራምፕ ያቀረቡትን ፍልስጤማውያን ከጋዛ የማስወጣት ሀሳብ በፍጹም እንደማይቀበሉት ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በጻፉት ደብደባ ግልጽ አድርገዋል።
በግብጽና ኳታር አደራዳሪነት ለ15 ወራት የዘለቀውን ጦርነት ያስቆመው የእስራኤል-ሀማስ የተኩስ አቁም ስምምት የተወሰኑ ታጋቾች በፍልስጥኤማውያን እስረኞች እንዲለዋወጡ ቢያስችለም ቀጣይነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
ሀማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ 1200 ሰዎችን ከገደለና 250 ሰዎችን ካገተ በኋላ እስራኤል በወሰደችው መጠነሰፊ ጥቃት ከ47 ሺ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። እስራኤል በጋዛ የዘረ ማጥፋት ፈጽማለች በሚል የቀረበባትን ክስ አስተባብላለች
ሀገራቱ ፍልስጤማውያን በመልሶ ግንባታው ተሳታፊ መሆን እንደሚገባቸውና መፈናቀል እንደሌላቸው እንደሚፈልጉ እየገለጹ ናቸው።