አንድ ሚሊዮን ዩክሬናዊያን የሩሲያን ጦር እየተዋጉ እንደሆነ ተገልጿል
ዩክሬን ዘጠኝ ሺህ ወታደሮቿ በሩሲያ ጦር እንደተገደሉባት ገለጸች።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ከጀመረች ዛሬ ስድስት ወራት አስቆጥሯል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት ከ10 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ሲሰደዱ በዓለም ላይ ደግሞ የነዳጅ እና ምግብ ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል።
የዩክሬን መከላከያ ዋና አዛዥ ቫለሪ ዛሉዚኒ ስድስት ወራት ባስቆጠረው ጦርነት ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዋና አዛዡ በመግለጫቸው እስካሁን ዘጠኝ ሺህ የዩክሬን ወታደሮች በሩሲያ ጦር መገደላቸውን ተናግረዋል ብሎ ሮይተርስ ዘግቧል።
አሁን ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዩክሬናዊያን ህጻናት ደህንነት ይፈልጋሉ ያሉት አዛዡ የሩሲያ ጥቃት በሁሉም የዩክሬን ከተሞች ሊፈጸሙ ይችላሉም ብለዋል።
የዩክሬን ጦር አባላት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ45 ሺህ በላይ የሩሲያ ወታደሮችን እንደገደሉም ዋና አዛዡ ተናግረዋል።
ሀገራቸውን ከሩሲያ ለመጠበቅም አንድ ሚሊዮን ዩክሬናዊያን በሁሉም ግንባሮች ከሩሲያ ጦር ጋር እየተዋጉ እንደሆነም አዛዡ አክለዋል።
አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ ሀገራት በሩሲያ ላይ ማዕቀቦችን በመጣል ላይ ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ በመለገስ ላይ ናቸው።
አሜሪካ ከሰሞኑ ለዩክሬን ተጨማሪ 800 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያ ድጋፍ አጽድቃለች።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሩሲያ ጋር ቀጥታ ጦርነት ውስጥ ላለችው ዩክሬን ተጨማሪ 800 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ፈርመዋል።
አሜሪካ የጦር መሳሪያውን ድጋፍ ያደረገችው ዩክሬን የኑክሌር ጥቃት ከሩሲያ ሊያጋጥማት ይችላል በሚል ነው።