ሶማሊያ የሽብር ጥቃትን ቀድመው ያልተከላከሉ የሥራ ኃላፊዎችን እንደምትጠይቅ ገለጸች
የሀገሪቱ ፖለቲከኞች፤ መንግስት የሃያት ሆቴልን በአስቸኳይ ከአልሸባብ ነጻ አላደረገም ሲሉ ወቅሰዋል
በጥቃቱ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባቸው ከሶማሊያ ውጭ ባሉ ቦታዎች ይታከማሉ ተብሏል
ሶማሊያ ከሰሞኑ በዋና ከተማዋ የደረሰውን የሽብር ጥቃት ቀድመው ያልተከላከሉ የሥራ ኃላፊዎች እንደሚጠየቁ አስታወቀች።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ ባሬ፤ በሞቃዲሾ ሃያት ሆቴል የደረሰውን የሽብር ጥቃት ቀድመው ያልተከላከሉ ባለስልጣናት ተጠያቂ እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከጥቃቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ ባሬ፤ መግለጫውን የሰጡት የጸጥታ ኃይሎች የሃያት ሆቴልን ከአልሸባብ ነጻ ካወጣ በኋላ ነው፡፡ የሶማሊያ የጸጥታ ሹሞች 35 ሰዓትን የፈጀ ወታደራዊ ተልዕኮ በማካሄድ የሞቃዲሾውን ጥቃት ማክሸፋቸውን ገልጸዋል፡፡
“ይህንን አይነት የሽብር ጥቃት በድጋሚ እንዲከሰት አንፈልግም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣትና ቸልተኛ በመሆን ጥቃቱን መከላከል ባልቻሉ ሹሞች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡
የሶማሊያ የጤና ሚኒስትር አሊ ሃጂ አደን በሃያት ሆቴል በደረሰው ጥቃት 21 ሰዎች መገደላቸውንና 117 ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ባሬ አልሸባብ እንዳደረሰ በተገለጸው ጥቃት የተጎዱ ዜጎችን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጥቃቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ከሀገሪቱ ውጭ ባሉ የህክምና ተቋማት ለማሳከም እንደታሰበም ተገልጿል፡፡ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች፤ መንግስት የሃያት ሆቴልን በአስቸኳይ ከአልሸባብ ነጻ ማድረግ አልቻለም የሚል ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡
አልሸባብ በሶማሊያ መዲና የሽብር ጥቃት ሲፈጽም ከአዲሱ ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ መሐመድ ሹመት በኋላ የመጀመሪያው ነው፡፡