ኳታር በጋዛ ለሶስት ቀናት ተኩስ እንዲቆም እያደራደረች ነው ተባለ
እስራኤል ተኩስ ስታቆም ሃማስ 50 ታጋቾችን እንዲለቅ ነው ድርድር እየተደረገ የሚገኘው
ድሃ በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ተደማጭነት ያላት ሸምጋይ ሀገር ሆናለች
ኳታር በጋዛ የሶስት ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እያደራደረች መሆኑ ተገለጸ።
እስራኤል 41ኛ ቀኑን የያዘውን የጋዛ ጦርነት ለሶስት ቀናት ካቆመች ሃማስ 50 ሲቪል ታጋቾችን ይለቃል መባሉንም ነው ሬውተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ የዘገበው።
አሜሪካም እየተሳተፈችበት ያለው ድርድር እስራኤል ሴቶች እና ህጻናት ፍልስጤማውያንን ከእስርቤቶቿ እንድትለቅ የሚጠይቅ ሃሳብ ማካተቱም ተገልጿል።
ሃማስ በመሰረታዊ የድርድር ነጥቦቹ ላይ መስማማቱ የተገለጸ ሲሆን፥ በዝርዝር ነጥቦች ላይ መደራደሯን የቀጠለችው እስራኤል ስለመስማማቷ ያለችው ነገር የለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለፈው ሳምንት ከአሜሪካው ኤንቢሲ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ግን ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከሃማስ ጋር ድርድር እየተደረገ መሆኑን ፍንጭ መስጠታቸው ይታወሳል።
ሃማስ 50 ታጋቾችን እንዲለቅ የሶስት ቀናት ተኩስ አቁም ይደረግ ስለሚለው የኳታር እና አሜሪካ መር ድርድር ግን ቴል አቪቭ ዝምታን መርጣለች።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋንዝ ግን ሀገራቸው ታጋቾችን ለማስለቀቅ በጋዛ ጦርነቱን እንድታቆም ጥያቄዎች ቢበዙም “አላማችን ሳናሳካ የሚቆም ጦርነት” የለም ሲሉ ተናግረዋል።
እስራኤላውያን የታጋች ቤተሰቦች በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መኖሪያ አቅራቢያ በማምራት የሚያሰሙትን ተቃውሞ መቀጠላቸውም ተገልጿል።
የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ መቀመጫዋ ዶሃ በጋዛ ተኩስ እንዲቆምና በሃማስ የታገቱ ከ240 በላይ ታጋቾችን እንዲለቀቁ ጥረት ከጀመረች ዋል አደር ብላለች።
ከእስራኤልም ሆነ ከሃማስ ጋር የቀጥታ ግንኙነት ያላት ዶሃ እስራኤል በቀን ለአራት ስአት በጋዛ ተኩስ ለማቆም ስትስማማም ከፍተኛ ሚና እንደነበራት የሚታወስ ነው።
የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ አል ቃሳም ብርጌድ ከቀናት በፊት እስራኤል ለአምስት ቀናት ተኩስ ካቆመች 70 ታጋቾችን ለመልቀቅ ፈቃደኛ መሆኑን ለኳታር መግለጹ ይታወሳል።
እስራኤል ግን በሃማስ ላይ ጫናውን በማበርታት ታጋቾችን ለማስለቀቅ ጥረት ማድረግን የመረጠች ይመስላል።