በእስራኤል ጦር የተገደሉ ፍልስጤማዊያን ደግሞ ወደ 3 ሺህ 500 አሻቅቧል
በሀማስ የተገደሉ የእስራኤል ወታደሮች ቁጥር 306 መድረሱ ተገለጸ።
ከሁለት ሳምንት በፊት የተጀመረው የእስራኤል-ፍልስጦም ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል።
ይህ ጦርነት ከሀገራት አልፎ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ዋነኛንመነጋገሪያ አጀንዳ እንደሆነ ቀጥሏል።
የእስራኤል መከላከያ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ በሀማስ ጥቃት የተገደሉ እስራኤላዊያን ወታደሮች ቁጥር ወደ 306 ከፍ ብሏል።
ህይወታቸው ያለፉ ወታደሮች ቤተሰቦቻቸው እንዲያውቁት ተደርጓል የተባለ ሲሆን 203 እስራኤላዊያን አሁንም በሀማስ እንደታገቱ ተገልጿል።
በሀማስ ጥቃት የቆሰሉ ዜጎች ቁጥር 4 ሺህ 629 ደርሷል የተባለ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 80ዎቹ በጽኑ ህክምና ክትትል ውስጥ ናቸውም ተብሏል።
በአጠቃላይ በሀማስ ጥቃት የተገደሉ እስራኤላዊያን ቁጥርም 1 ሺህ 400 ሲደርስ እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ደግሞ 3 ሺህ 500 ሙድረሱ ተገልጿል።
ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን በርካታ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እስራኤል ጥቃቷን እንድታቆም በማሳሰብ ላይ ናቸው።
የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት እስራኤል ጦርነቱን እንድታቆም በሚል ቡቀረበው ሀሳብ ላይ የተወያየ ቢሆንም በአሜሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ምክንያት ሀሳቡ ውድቅ መደረጉ ተገልጿል።
አሜሪካ በግልጽ እና በቀጥታ ለእስራኤል ድጋፍ በማድረግ ላይ ስትሆን ኢራን በበኩሏ እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ጥቃት እንድታቆም አስጠንቅቃለች።