ግብጽ የእስራኤልን እቅድ በፍጹም እንደማትቀበል አስታውቃለች
ግብጽ ለሲናይ በረሀ ስትል ሚሊዮኖችን እንደምታሰልፍ ገለጸች።
የእስራኤ-ሀማስ ወይም ፍልስጤም ጦርነት ከተጀመረ 25ኛ ቀኑ ላይ የሚገኝ ሲሆን አሁንም እልባት አልተገኘለትም።
የዓለምን ትኩረት የሳበው ይህ ጦርነት በየዕለቱ አዳዲስ ክስተቶችን እያስተናገደ ሲሆን እስራኤል በፍልስጤማዊያን ላይ እያደረሰች ያለውን ጥቃት እንድታቆም ግፊቱ ቀጥሏል።
የእስራኤል ደህንነት 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ፍልስጤማዊያንን ወደ ሲናይ በረሀ የማዛወር እቅድ እንዳለው ግብጽ አስታውቃለች።
የግብጽ ጠቅላይ ሚንስትር ሞስጠፋ ማድቡሊ እንዳሉት "ግብጽ ለሲናይ በረሀ ስትል ሚሊዮኖችን ታሰልፋለች" ብለዋል።
እንደ አልአረቢያ ዘገባ ግብጽ የእስራኤል ደህንነትን እቅድ ፈጽሞ አትቀበልም ያሉ ሲሆን ለሲናይ በረሀ ስትልም ሚሊዮን ዜጎቿን ለማሰለፍ እና ለመገበር ዝግጁ ማለታቸው ተገልጿል።
የመካከለኛው ምስራቅ ችግር በግብጽ መስዋዕትነት ሊፈታ አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ የእስራኤልን እቅድ ውድቅ አድርገዋል።
ፍልስጤማዊያንን ወደ ሲናይ በረሀ የማዛወር የእስራኤል እቅድ ከወዲሁ ከግብጽ እና ከሌሎች ሀገራት ውግዘት ገጥሞታል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ውግዘት የገጠመው እቅዳቸው በይፋ የሀገሪቱ አቋም እንዳልሆነ በመግለጽ እየደረሰባቸው ያለውን ትችት ለማለስለስ መሞከራቸው ተገልጿል።
ግብጽ የጋዛ ቀውስ ወደ ሀገሯ እንዳይገባ ስጋት እንዳላት በመገለጽ ላይ ሲሆን በርካታ ሌሎች ሀገራትም ቀውሱ ወደ ጎረቤት ሀገራት ሊስፋፋ ይችላል በሚል በማሳሰብ ላይ ናቸው።
እስራኤል ባደረሰች ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማዊያን ቁጥር በየሰዓቱ በመጨመር ላይ ሲሆን እስካሁን 8300 ሰዎች ተገድለዋል።
በሀማስ ጥቃት የተገደሉ እስራኤላዊያን ቁጥር ደግሞ 1ሺህ 400 መድረሱ ተገልጿል።