በስምምነት መሰረት ሁለቱም አካላት ለአምስት ቀናት ውጊያ ሲያቆሙ ቢያንስ 50 የሚሆኑ ታጋቾች ይለቀቃሉ
እስራኤል፣ ሀማስ እና አሜሪካ ጊዜያዊ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ።
እስራኤል፣ ሀማስ እና አሜሪካ ጦርነቱን በጊዜያዊነት ጋብ ለማድረግ እና በደርዘን የሚቆጠሩ ታጋቾችን ነጻ ለማድረግ ጊዚያዊ የሆነ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ሮይተርስ ዋሽንግተን ፖስትን ጠቅሶ ዘግቧል።
ለአምስት ቀናት ተኩሱ ጋብ እንዲል በተደረገው ስምምነት የሚለቀቁት ታጋቾች ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
እንደዘገባው ከሆነ ስድስት ገጽ ባለው ስምምነት መሰረት ሁለቱም አካላት ለአምስት ቀናት ውጊያ ሲያቆሙ ቢያንስ 50 የሚሆኑ ታጋቾች በየ24 ሰአቱ በተለያዩ ትናንሽ ቡድኖች ሆነው ይለቀቃሉ።
ስምምነቱ ተግባራዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የአየር ላይ ቅኝት እንደሚካሄድም ተገልጿል።
ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር የእስራኤልን ድንበር በመጣስ እጅግ ከባድ እና ያልተጠበቀ ጥቃት አድርሶ 1200 ሰዎችን ከገደለ እና 240 የሚሆኑትን ካገተ በኋላ እስራኤል በሀማስ ይዞታ በሆነችው ጋዛ ላይ ሙሉ ጦርነት ከፍታለች።
እስራኤል እየወሰደችው ባለው የእግረኛ እና የአየር ጥቃት እስካሁን ከ11ሺ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከአራት ሳምንታት በላይ ሆኖታል።
በጋዛ ተኩስ እንዲቆም የሰብአዊ ድርጅቶች እና በርካታ ሀገራት ቢጠይቁም፣ እስራኤል እና አጋሯ አሜሪካ ሳይቀበሉት ቆይተዋል።