አንድ እስራኤላዊ ታጋች መሞቱን የሀማስ ወታደራዊ ክንፍ አስታወቀ
የጋዛ የጤና ባለስልጣናት አንደሚሉት ከሆነ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 31ሺ ደርሷል
የሀማስ ታጣቂ ክንፍ አል ቃሰም ብርጌድ እንዳስታወቀው አንድ የ34 አመት እስራኤላዊ ታጋች "በመድሃኒት እና ምግብ እጥረት" ምክንያት ህይወቱ አልፏል
የሀማስ ታጣቂ ክንፍ አል ቃሰም ብርጌድ ባለፈው ቅዳሜ እለት እንዳስታወቀው አንድ የ34 አመት እስራኤላዊ ታጋች "በመድሃኒት እና ምግብ እጥረት" ምክንያት ህይወቱ አልፏል።
ብርጌዱ የጂቭ ቡካታፍ የተባለ የ34 አመት ጽዮናዊ መሞቱን በቴሌግራም ገጹ በለቀቀው የቪዲዮ መልክት ገልጿል።
ብርጌዱ በዚህ መግለጫው ቀደም ሲል የእስራኤል ታጋቾች እንደፍልስጤማውያን ሁሉ በምግብ እና በመድሃኒት እጥረት እየተሰቃዩ እንደነበር መግለጹን አስታውሷል።
"የጋዛ ህዝብን እያሰቃየ ያለው ከበባ፣ የምግብ እና የመድሃኒት እጥረት የጠላት(የእስራኤል) ታጋቾችንም እያሰቃየ ነው" ያለው ብርጌዱ ይህ ታጋች ከእስራኤል የአየር ጥቃት ቢያመልጥም በምግብ እና መድሃኒት እጥረት ከመሞት አልዳነም ብሏል።
እስራኤል እና ሀማስ የታጋቾችን መለቀቅ ያካተተ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ግብጽ፣ ኳታር እና አሜሪካ ጥረት ቢያደርጉም እስካሁን አልተሳካም።
ባለፈው ህዳር ወር በኳታር አደራዳሪነት በተደረሰው ተኩስ ጋብ የማድረግ ስምምነት ሀማስ የተወሰኑ ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል በምላሹ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፍልስጤም እስረኞችን መልቀቋ ይታወሳል።
ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር የእስራኤልን ድንበር ጥሶ ባደረሰው ከባድ ጥቃት 240 ሰዎችን ማገቱን እና 1200ሰዎች መግደሉን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ መጠመሰፊ ጥቃት እያካሄደች ትገኛለች።
የጋዛ የጤና ባለስልጣናት አንደሚሉት ከሆነ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 31ሺ ደርሷል።