ማሻሻያውን ተከትሎ በመቶ ሚሊየን የሚቆጠር ዶላር በግብፅ ባንኮች መንቀሳቀስ ጀምሯል
ግብጽ የገንዘቧን የመግዛት አቅም በ13 በመቶ ማዳከሟን ተከትሎ የዶላር ፍሰቱ መጨመሩ ተነገረ።
የሀገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ታሪካዊ ነው የተባለውን ማሻሻያ በማድረጉ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ32 ነጥብ 2 የግብፅ ፓውንድ እየተመነዘረ ነው።
ከትናንት በስቲያ ተግባራዊ የተደረገውን የምንዛሬ ለውጥ ተከትሎ በመቶ ሚሊየን የሚቆጠር ዶላር በግብፅ ባንኮች መንቀሳቀስ መጀመሩን የሀገሪቱ የዜና ወኪል ሜና ያነጋገራቸው የባንክ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ረቡዕ ብቻ 800 ሚሊየን ዶላር በግብፅ ባንኮች መንቀሳቀሱ ነው የተገለፀው።
በባንኮቹ የታየው መነቃቃት አለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ለካይሮ ገንዘብ ለመልቀቅ እንዲዘጋጁ ያደርጋቸዋል ተብሏል።
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የቱሪዝም ገቢዋን ክፉኛ የጎዳባት ግብጽ፥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አጋጥሟታል።
የግብጽፓውንድ የምንዛሬ አቅም ካለፈው አመት መጋቢት ወር ወዲህ በ51 በመቶ መውረዱን ሬውተርስ ዘግቧል።
ከሰሞኑ የተደረገው የፓውንድ የመግዛት አቅም መዳከምም በባንክ ስርአት ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ዶላር መጠን እጅግ እንዲጨምር አድርጎታል ነው የተባለው።
ባለፉት ሁለት ቀናት ከ650 እስከ 750 ሚሊየን ዶላር ፍሰት መታየቱን የግብፅ ባንኮች አረጋግጠዋል።
የግብጽ ፓውንድ የመግዛት አቅም በ13 በመቶ መዳከሙ በግብፃውያን የእለት ተዕለት ኑሮ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ግን አልተጠቀሰም።