አልሲሲ በታህሳሱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እጩ ሆነው እንደሚፎካከሩ ይፋ አደረጉ
ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህህ አልሲሲ ፥ ምርጫው “የእውነተኛና ሁሉን አካታች ፖለቲካ ጅማሮ” እንደሚሆን ገልጸዋል
አልሲሲ ቻይናን እንደአብነት በማንሳት “ረሃብና ችግርን ታግሰን እንለፈው” የሚል አስተያየት መስጠታቸው ግብጻውያንን አስቆጥቷል
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በታህሳስ ወር በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚፎካከሩ ይፋ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ምርጫ “እኔን ባትመርጡኝም’ በነቂስ ወጥታችሁ ድምጻችሁን ስጡ የሚል መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።
የ68 አመቱ አልሲሲ ለሶስተኛ እና የመጨረሻው የስልጣን ዘመን እንደሚፎካከሩ ያስታወቁት በአዲሷ ካይሮ ነው።
በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸውም አልሲሲ በምርጫው እንደሚሳተፉ በይፋ ሲገልጹ በአደባባይ ደስታቸውን ሲገልጹ የሚያሳዩ ምስሎችን የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ አሳይቷል።
ፕሬዝዳንቱ ምርጫው “የእውነተኛና አካታች ፖለቲካ ጅማሮ” ማብሰሪያ ይሆናል ሲሉም ተፎካካሪዎቻቸውን አድንቀዋል።
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው አብዱልፈታህ አልሲሲ ማሸነፋቸው እንደማይቀር የብዙዎች እምነት ነው የሚለው ፍራንስ24፥ የቀድሞው የፓርላማ አባል አህመድ አል ታንታዊ ዋነኛ ተቀናቃኛቸው እንደሚሆኑ ገልጿል።
አል ታንታዊ በምርጫው ለመሳተፍ ከ25 ሺህ ግብጻውያን የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ይጠበቅባቸዋል።
የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላትን በማሰር ምርጫው የአንድ ፈረስ ሩጫ እንዲሆን አድርጓል በሚል የሚተቸው የአልሲሲ አስተዳደር የታህሳሱ ምርጫ ካለፉት ሁለት ምርጫዎች የተሻለ ፉክክር እንዲኖረው ፍላጎት እንዳለው ሲገልጽ ይደመጣል።
ይሁን እንጂ ለአልሲሲ ሶስተኛውና የመጨረሻው የስልጣን ዘመናቸው ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከባድ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ የሚጠበቅ አይደለም ነው የተባለው።
አልሲሲ ከሰሞኑ 39 ነጥብ 7 የደረሰው የዋጋ ግሽበት የሚቀንስበትን መንገድ ከመጠቆም ይልቅ ታግሰን እንለፈው የሚል አስተያየት መስጠታቸው ግብጻውያንን አስቆጥቷል።
“ልማትና እድገት ረሃብና ችግር ቢያመጣ እንኳን ምግብ ይቅደም ማለት የለብንም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ቻይናን እንደ አብነት አንስተዋል።
“ቻይና 25 ሚሊየን ሰዎችን በረሃብ አጥታ ነው ታላቅ ሀገር የሆነችው” በማለትም የኑሮ ጫና ጋር ተያይዞ የሚነሳባቸውን ትችት ለመከላከል ሞክረዋል።
የአለም ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው ከወቅታዊው የኢኮኖሚ ቀውስ በፊት ከግብጽ ህዝብ ሲሶው ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ነው።
የሀገሪቱ የውጭ ብድር ጫናም 165 ቢሊየን ዶላር ደርሷል።
ለዚህም ለአዲሷ መዲና ካይሮ ግንባታ የወጣውን 58 ቢሊየን ዶላር ጨምሮ ለቅንጡ ፕሮጀክቶች እና መንገድ ግንባታዎች ከፍተኛ ወጪ መውጣቱን የሚቃወሙ በርካታ ናቸው።
የብሉምበርግ መረጃ እንደሚያሳየው ግብጽ ከዩክሬን በመቀጠል እዳዋን ለመመለስ የምትቸገር ሀገር ሆናለች።
ሞሃመድ ሙርሲን በ2013 በሃይል በማንሳት ስልጣን የተቆጣጠሩት አብዱልፈታህ አልሲሲ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ሲመረጡ ቀውስ ውስጥ ያለውን ኢኮኖሚ እንዴት ሊያረጋጉት ይችላሉ የሚለው አጠያያቂ ነው።