ስዊዝ ካናል አገልግሎት መስጠት ከጀመረ 153 ዓመት ሞልቶታል
ግብጽ ከስዊዝ ካናል ሰባት ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታገኝ ገለጸች፡፡
ከ153 ዓመት በፊት ሜድትራኒያን ባህርን እና ህንድ ውቂያኖስን በማገኛኘት በአውሮፓ እና እስያ መካከል የሚደረገውን የባህር ላይ ጉዞ በማሳጠር ዘመናዊ የባህር ትራንስፖርት ያቀላጥፋል፡፡
የግብጽ ዓመታዊ በጀት ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን በጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ብቻ ይቀረዋል፡፡
የሀገሪቱ ገንዘብ ሚኒስትር መሀመድ ባይት ለብዙሃን መገናኛዎች በሰጡት መግለጫ ግብጽ ካሳለፍነው ሀምሌ ጀምሮ እስከ ሰኔ ባሉት 12 ወራት ውስጥ ከስዊዝ ካናል 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታገኝ ተናግረዋል፡፡
የግብጽ ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆነው የስዊዝ ካናል በፈረንጆቹ 1869 ዓመት ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት የሆነ ሲሆን ይህ የመርከቦች መጓጓዣ መስመር በቀን 50 መርከቦችን በማጓጓዝ ላይ ይገኛል፡፡
በወቅቱ የግብጽ መሪ የነበሩት ካዲቭ እስማኤል ፓሻ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይህ የመርከቦች መተላለፊያ መስመር ግንባታው 10 ዓመታትን ፈጅቷል፡፡
በዓመት 300 ሚሊዮን ቶን እቃዎች የሚተላለፉበት ስዊዝ ካናል የአገልግሎት መጠኑን ለማስፋት ግብጽ በየጊዜው የተለያዩ ማሻሻያዎችን አድርጋለች፡፡
የአሁኑ የግብጽ ፕሬዝዳንት አልሲሲ በፈረንጆቹ 2014 ላይ በስዊዝ ካናል ላይ የተደረገውን የ8 ቢሊዮን ዶላር የማስፋፋያ ግንባታ መመረቃቸው አይዘነጋም፡፡
ስዊዝ ካናል በተሰራለት የማስፋፊያ ግንባታ መሰረት አሁን ላይ ስፋቱ 61 ሜትር በ312 ሜትር ላይ የደረሰ ሲሆን ከአንድ ዓመት በፊት ከቻይና የመጣ ኮንቴይነሮችን የጫነች እቃ ጫኝ መርከብ መተላለፊያ መስመሩን ለአንድ ወር ዘግታ የ100 መርከቦችን እንቅስቃሴ በመግታት የዓለምን ንግድ ማስተጓጎሏ ይታወሳል፡፡