ግብጽ መርከቧ ላደረሰችባት ኪሳራ 900 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ጠይቃ ነበር
ስዊዝ ካናልን ለሳምንት ዘግታ ታግታ የነበረችው ኤቨር ጊቭን መርከብ መንቀሳቀስ ጀመረች።
መርከቧ ዓለም አቀፉን የሎጂስቲክስ መስመር ለአንድ ሳምንት ከዘጋች በኋላ በግብጽ ላደረሰችው ኪሳራ ካሳ መከፈል አለበት በሚል አለመግባባት እስካሁን መቆየቷን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
መርከቧ በፈረንጆቹ ከመጋቢት 23 አስከ 29 2021 ዓመት ባሉት ስድስት ቀናት ላደረሰችው ኪሳራ የግብጽ መንግስት ያቀረበው የካሳ ክፍያ መጠን እና ኩባንያው ጥያቄው ተጋኗል በሚል ሳይግባቡ ቆይተዋል።
የስዊዝ ካናል ባለስልጣን ኤቨር ጊቭን መርከብ ላደረሰብኝ ኪሳራ 900 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፈለው ጠይቆ ነበር።
የመርከቧ ባለቤቶች ግን የካሳ ጥያቄው ተጋኗል በሚል በተደረጉ ድርድሮች የሲዊዝ ካናል ባለስልጣን የካሳ ክፍያውን ወደ 550 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ማድረጉን ዘገባው ጠቅሷል።
አሁን ላይ በተደረገ የመጨረሻ ዙር ድርድር ሁለቱ አካላት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ መርከቧ ከግብጽ ለመውጣት በጉዞ ላይ መሆኗ ተገልጿል።
ይሁንና የመርከቧ ባለቤቶች ለስዊዝ ካናል ባለስልጣናት መርከቧ እንድትለቀቅላቸው ምን ያህል ገንዘብ እንደከፈሉ እስካሁን አልተጠቀሰም።
ስዊዝ ካናል የዓለማችን 15 በመቶ የንግድ እንቅስቃሴ የሚተላለፍበት ሲሆን በተለይም በአውሮፓ እና አስያ መካከል የሚደረጉ የንግድ ልውውጦችን ያቀላጥፋል።