እስራኤል እና ፍልስጤም በአል አቅሳ መስጂስ በረመዳን እና ፋሲካ ወቅት መረጋጋት እንዲኖር ተወያዩ
ውይይቱ የአንድ ወገን እርምጃዎችን ለማስቆም ያለመ ነው ተብሏል
ባለፉት ዓመታት በእየሩሳሌም አል አቅሳ መስጊድ በረመዳንና በፋሲካ በዓል ወቅት በእስራኤል ፖሊሶች እና በፍልስጤማውያን መካከል ግጭት ተቀስቅሷል
እስራኤል እና ፍልስጤም በአል አቅሳ መስጂስ በረመዳን እና ፋሲካ ወቅት መረጋጋት እንዲኖር ተወያዩ
ግብጽ የእስራኤል እና የፍልስጤም ባለስልጣናትን በሻርም ኤል ሼክ ከተማ አስተናግዳለች።
ውይይቱ በአሜሪካ እና ዮርዳኖስ የተደገፈና የረመዳን ወር ከመጀመሩ በፊት ዌስት ባንክን ለማረጋጋት ዓላማ የሰነቀ ነው።
የአምስቱ ወገኖች ስብሰባ በዮርዳኖስ በአሜሪካ አደራዳሪነት የተካሄደው የየካቲት ስብሰባ ተከታይ ነው ተብሏል።
በዮርዳኖስ የተካሄደውና በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ስብሰባ፤ እስራኤል እና ፍልስጤም ውጥረቱን ለማርገብ ቃል የገቡበት ነው።
ነገር ግን ስምምነቱ በሁለቱም ወገን ባሉ አንጃዎች ተቃውሞ ገጥሞታል።
በመሆኑም ስምምነቱ በሀገራቱ ላይ ያለውን ብጥብጥ ማስቆም አልቻለም ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
በሻርም ኤል ሼክ የተካሄደው ስብሰባ “በፍልስጤም እና በእስራኤል ወገኖች መካከል የአንድ ወገን እርምጃዎችን ለማስቆም፣ ነባሩን የጥቃት አዙሪት ለመስበር እና መረጋጋትን ለመፍጠር ያለመ ነው” ሲል የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገልጿል።
ይህም "የሰላሙን ሂደት እንደገና ለማስጀመር ተስማሚ ከባቢን ሊያመቻች ይችላል" ሲል አክሏል።
ፍልስጤማውያን በዌስት ባንክ እና በጋዛ ሰርጥ ነጻ መንግስት ለመመስረት ዓላማ ያላቸው ሲሆን፤ እስራኤል በ1967 ጦርነት የማረከችውን ግዛት ምስራቅ እየሩሳሌምን ዋና ከተማ የማድረግ ፍላጎት አላቸው።
ነገር ግን ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ የሰላም ድርድሩ ቆሞ ቆይቷል።
ፍልስጤማውያን የአይሁዶች የሰፈራ መስፋፋት ብቁ ሀገር የመመስረት እድልን ጎድቶታል ይላሉ።
ቀደም ባሉት ዓመታት በእየሩሳሌም አል አቅሳ መስጊድ በረመዳን መግቢያ አካባቢና ከፋሲካ በዓል ላይ በእስራኤል ፖሊሶች እና በፍልስጤማውያን መካከል ግጭት ይቀሰቀሳል።