የአሜሪካ፣ የዮርዳኖስ እና የግብጽ ከፍተኛ ባለስልጣናት በውይይቱ እንደተሳተፉ ታውቋል
እስራኤል እና ፍልስጤም ሁከትን ለመግታት ቃል ገቡ።
የእስራኤል እና የፍልስጤም ባለስልጣናት እየጨመረ ያለውን ግጭት ለማርገብ ቃል ገብተዋል።
ሀገራቱ ባወጡት የጋራ መግለጫ እስራኤል በተያዘው ዌስት ባንክ አዳዲስ ሰፈራዎችን ለአራት ወራት ያህል እንደምታቆም ገልጻለች።
ከእስራኤል እና የፍልስጤም ልዑካን በተጨማሪ የአሜሪካ፣ የዮርዳኖስ እና የግብጽ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተሳተፉበት በአቃባ ዮርዳኖስ የተደረገው ስብሰባ በአይነቱ ከዓመታት በኋላ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
የእስራኤል እና የፍልስጤም ወገኖች በመግለጫቸው "ተጨማሪ ጥቃትን" ለመከላከል በቅርበት እንደሚሰሩ እና "በመሬት ላይ ያለውን ግጭት ለማርገብ ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑን አረጋግጠዋል" ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ሀገራቱ ከዚህ ቀደም ለተደረጉ ስምምነቶችም ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል ተብሏል።
ዮርዳኖስ ከአጋሮቿ ግብጽ እና አሜሪካ ጋር በመሆን "በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ግንኙነት እንደገና ለማደስ እና ለማጠናከር ስምምነት ላይ ተደርሷል" ብለዋል።
ሆኖም የጋዛ ሰርጥን የሚያስተዳድረው የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ ስብሰባውን “ዋጋ ቢስ” ሲል የጠራ ሲሆን፤ በዌስት ባንክ የተመሰረተውን የፍልስጤም አስተዳደር በመሳተፉ አውግዟል።
ስብሰባው የተካሄደው በመጪው መጋቢት በሚጀመረው የቅዱስ ረመዳን ወር ሁከት ስጋት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ነው።