ግብጽ በቀይ ባህር ቀውስ ምክንያት በየወሩ ከ370 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እያጣሁ ነው አለች
ሀገሪቱ ከዚህ በፊት ከስዊዝ ካናል በየወሩ በአማካኝ 800 ሚሊዮን ዶላር ስታገኝ ነበር
የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት የዓለም ባህር ትራንስፖርት ዋጋ እንዲያሻቅብ አድርጓል
ግብጽ በቀይ ባህር ቀውስ ምክንያት በየወሩ ከ370 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እያጣሁ ነው አለች፡፡
አራት ወራት ሊሆኑት ሶስት ቀናት ብቻ የቀረው የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት መቋጫ ያላገኘ ሲሆን የዓለምን ኢኮኖሚ በመጉዳት ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ጦርነት አሜሪካ ለእስራኤል የቀጥታ ድጋፍ ማሳየቷን ተከትሎ የየመን ሂቲ አማጺያን ከእስራኤል እና አሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች በመምታት ላይ ናቸው፡፡
ይህንን ተከትሎም የቀይ ባህር ትራንስፖርት በስጋት እንዲሞላ በማድረጉ የዓለም ሎጅስቲክስ ኩባንያዎች ይህን የንግድ መስመር ከመጠቀም እየተቆጠቡ ይገኛሉ፡፡
የግብጹ ስዊዝ ካናል ዋነኛ የመርከቦች መተላለፊያ ሲሆን በቀይ ባህር ቀውስ ምክንያት ያስተናግዳቸው የነበሩ ደመርከቦች መቀነሳቸው ተገልጿል፡፡
አዲሱ የፈረንጆቹ 2024 ከገባ ወዲህ ባሉት ቀናት ያስተናገዳቸው መርከቦች ቁጥር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ46 በመቶ ቅናሽ ማሳየታቸውን አልአረቢያ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ስዊዝ ካናል የሚያስተናግዳቸው መርከቦች ቁጥር በ30 በመቶ እንደቀነሰ የስዊዝ ካናል ባለስልጣን ሀላፊ ኦሳማ ራቢ ተናግረዋል፡፡
ግብጽ ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ 804 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታ የነበረ ሲሆን ይህ ገቢ ወደ 428 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል፡፡
በቀይ ባህር ትራንስፖርት ቀውስ ምክንያት ግብጽ ከስዊዝ ካናል የምታገኘው ገቢ በ46 በመቶ ሲቀንስ የመርከቦች ቁጥር ደግሞ የ36 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል ተብሏል፡፡
የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት በቶሎ እልባት ካልተበጀለት የዓለምን ንግድ የበለጠ ሊጎዳው እንደሚችልም ተሰግቷል፡፡
ስዊዝ ካናል የግብጽ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ሲሆን በየዓመቱ የምታገኘው ገቢ በየጊዜው እየጨመረ በመምጣት ላይ እንደነበርም ተገልጿል፡፡
ግብጽ ከስዊዝ ካናል ባሳለፍነው 2023 ዓመት 9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ስታገኝ በ2022 ደግሞ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታበት ነበር፡፡
የዓለምን ንግድ በማሳለጥ የሚታወቀው የስዊዝ ካናል በዓመት 25 ሺህ መርከቦች የሚመላለሱበት ሲሆን ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ቶን በላይ እቃም ይጓጓዝበታል፡፡
በቀይ ባህር ባጋጠመው ቀውስ ምክንያት የዓለም የመርከብ እቃ ማጓጓዣ እና የመድህን ዋጋ በሶስት እጥፍ አሻቅቧል የተባለ ሲሆን ቀውሱ እልባት ካልተበጀለት የዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ የበለጠ እንዲጨምር ያደርጋልም ተብሏል፡፡