ሶማሊላንድ ለግብጽ ፕሬዝዳንት ንግግር በሰጠችው ምላሽ ምን አለች?
ሶማላሊላንድ መንግስት “የትኛውንም የውጭ አካል ጣልቃ ገብነት አጥብቀን እንቃወማለን” ብሏል
ሶማላሊላንድ “ግብጽ የዲፕሎማሲ ጥረቷን የጎረቤቶቿ የሱዳን፣ ሊቢያና ጋዛ ጦርነትን ለመፍታት እንድታውል” መክራለች
ሶማሊላንድ የግብጽ ፕሬዝዳንት ከሰሞኑ በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ የመግባቢያ ሰምምነትን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ዙሪያ በሰጠችው ምላሽ የትኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነት አጥብቃ እንደምትቃወም አስታውቃለች።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱን ተከትሎም ሶማሊላንድ የግዛቴ አንድ አካል ናት የምትላት ሶማሊያ የዲፕሎማሲ የበላይነት ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።
- ግብጽ ከሶማሊያ ጥያቄ ከቀረበላት ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች
- የሶማሊያ አጋር ለመምሰል የሚታዩ አጉል ጀብደኝነቶች ያለውን ውጥረት የሚያባብሱ ናቸው- ሬድዋን ሁሴን
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ በግብጽ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ ከግብጽ አቻቸው አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር ተወያይተው የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚሁ መግለጫም የግብጽ ፕሬዝዳንት አልሲሲ "የሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ የመግባቢያ ስምምነት ተቀባይነት የሌለው ነው፣ ከተጠየቅን ደግሞ በሶማሊያ ላይ የሚፈጸም የሉዓላዊነት እና ግዛት አንድነት ጥቃትን ለመመከት ድጋፍ እናደርጋለን" ብለዋል።
ይህንን ተከትሎ የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ያወጣ ሲሆን፤ በዚህም ለግብጽ ፕሬዝዳት አብዱልፈታህ አልሲሲ ዛቻ እና ማስፈራሪያ በሰጠው ምላሽ፤ “የየትኛውንም አካል የውጭ ጣልቃ ገብነት አጥብቀን እንቃወማለን” ብሏል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋሉ ክስተቶች አንፃር ሶማሊላንድ ቀጠናዊ ጉዳዮችን በውይይት እና በትብብር ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጣለች።
ሆኖም በሶማሊላንድ ሪፐብሊክ እና በኢትዮጵያ መካከል በተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ዙሪያ የሚደረግ ማንኛውንም የውጭ ጣልቃገብነት አጥብቃ እንደምትቃወምም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ሁሉም ፍላጎት ያላቸው አካላት ክልላዊ መረጋጋትን እና አጋርነትን ማጠናከር ላይ እንዲያተኩሩ እናበረታታለን ነው ያለው የሶማሊየ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።
ከዚህ አንጻር ግብፅ የዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን በቅርብ ጎረቤቶቿ ሱዳን፣ ሊቢያ እና ጋዛ ያሉ ግጭቶችን መፍታት ላይ እንድታውልም እናበረታታለን ብሏል ሚኒስቴሩ።
እነዚህ አካባቢዎች በአሁኑ ጊዜ ከከፍተኛ ችግር ጋር እየታገሉ ነው ያለችው ሶማሊላንድ፤ የግብፅ ተሳትፎ በሀገራቱ ዘላቂ ሰላም እና ደህንነት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል ብላ እንደምታምንም አስታውቃለች።
የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ መንግስት በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማትን ለማስፈን ከሁሉም ሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችን እና ትብብሮችን ማድረጉን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የግብጽ ፕሬዝዳት ንግግርን ተከትሎ በትናትናው እለት በኤክስ (X) ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ የሶማሊያ አጋር በመሆን መግለጫ እየሰጡ ላሉ አካላትን በስም ባይጠቅሱም፤ “አጀንዳቸው የምስራቅ አፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት አይደለም፤ እነሱ ሊዘሩት የሚፈልጉት ጠብ እና ትርምስ ነው” ሲሉ አስታውቀዋል።
“አሁን እያየን ያነው አጉል ጀብደኝነት ውጥረትን የሚያባብስ” እንዲሁም "ለአድርባይ የውጭ አካላት ጥቅም የሚመች" እንደሆነም አምባሳደር ሬድዋን ገልጸዋል።