ግብጽ በሀውቲ ታጣቂዎች ላይ ለመጨከን ትገደድ ይሆን?
ካይሮ ከ9 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ የምታስገባበትን የስዊዝ ቦይ ደህንነት ለማስጠበቅ ምን አይነት እርምጃ ልትወስድ ትችላለች?
የስዊዝ ቦይ የግብጽ የኢኮኖሚ ዋልታ ብቻ አይደለም፤ ቀጠናዊና አለማቀፋዊ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው
የየመኑ ታጣቂ ቡድን በቀይ ባህር ደቡባዊ ክፍል በሚጓዙ የንግድ መርከቦች ላይ የሚፈጽመው ጥቃት በርካታ የመርከብ ኩባንያዎች ከቀይ ባህር እንዲሸሹ እያደረገ ነው።
ይህ ውሳኔ ክፉኛ ከሚጎዳቸው ሀገራትም የሲዊዝ ቦይ መተላለፊያ ባለንብረቷ ግብጽ ቀዳሚዋ ናት።
እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመው ድብደባ ዋነኛ አላማው ፍልስጤማውያን ከጋዛ ወጥተው ወደ ግብጽ እንዲሸሹ ነው የምትለው ግብጽ፥ ቴል አቪቭን በመፋለም ላይ ለሚገኘው ሃማስ አጋር ከሆነው የሃውቲ ታጣቂ ቡድን ጋር ተፋጣለች።
ሳኡዲ መራሹን ሃይል ተቀላቅላ የየመኑን ታጣቂ ቡድን ለመፋለም በ2015 ወታደሮቿን ወደ ሰንአ የላከችው ካይሮ በቀይ ባህር የተጋረጠው አደጋ በቡድኑ ላይ ጦርነት እንድታውጅ ያስገድዳት ይሆን?
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠን በቀጣይ የምንመለከታቸው ቁጥሮች እና ታሪካዊ ሁነቶች ናቸው።
የስዊዝ ቦይ ምንድን ነው?
192 ኪሎሜትር የሚረዝመው የስዊዝ ቦይ (ካናል) እስያ እና አውሮፓን በአጭሩ የሚያገናኝ መተላለፊያ ነው።
ቦዩ በአለማችን እጅግ ወሳኝ ከሆኑ የንግድ መስመሮችና በባህር ወንበዴዎች ሊዘጉ ከሚችሉ ሰባት ወሽመጦች አንዱ መሆኑም ይነገራል።
9 በመቶ የሚሆነው የአለም ነዳጅ አቅርቦትም በስዊዝ ካናል በኩል ነው የሚያልፈው።
በ2023 የመጀመሪያ አጋማሽ በየቀኑ 9 ነጥብ 2 ሚሊየን በርሚል ነዳጅ በዚሁ ቦይ መተላለፉን የአሜሪካ የኢነርጂ መረጃ አስተዳደር ገልጿል።
በዚህ መተላለፊያ ከሚያልፉ መርከቦች የሚሰበሰበው ክፍያ የግብጽ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው፤ ካይሮ ከ9 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ታጋኝበታለች። ይህም ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷ ከ2 በመቶ በላዩን ይሸፍናል።
ቦዩ በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በኩል ይደረግ የነበረውን ጉዞ በማሳጠር ጊዜና ሃብትን ማዳን መቻሉም ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል።
ለአብነት ከታይዋን ኔዘርላንድስ በስዊዝ ቦይ በኩል 18 ሺህ 500 ኪሎሜትር ርቀት አለው፤ 25 ቀን ተኩልም ይወስዳል። በኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ ግን 25 ሺህ ኪሎሜትር የሚረዝም ሲሆን 34 ቀናትን ይፈጃል።
የመርከብ ኩባንያዎች ስጋት፤ የአሜሪካ መራሹ የባህር ቅኝት
ግዙፍ የመርከብ ኩባንያዎች የሃውቲ ታጣቂዎች ሊያደርሱት የሚችሉትን ጥቃት ሽሽት በቀይ ባህር መጓዝ እንደሚያቆሙ አሳውቀዋል።
የስዊዝ ካናል አስተዳደር ግን በርካታ መርከቦች በስዊዝ ቦይ መጓዛቸውን ስለመቀጠላቸው ነው የገለጸው። ከትናንት በስቲያ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስም 2 ሺህ 128 መርከቦች በቦዩ መጓዛቸውን አስታውቋል። በአንጻሩ ጉዟቸውን ወደ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ አዙረው የተጓዙት 55 መርከቦች ብቻ መሆናቸውን በመጥቀስ።
በጊዜያዊነት በቀይ መስመር አንጓዝም ያሉት የመርከብ ኩባንያዎች መርከቦችም በስዊዝ ቦይ በኩል እየተጓዙ ነው ብሏል የስዊዝ ቦይ አስተዳደር።
በአሜሪካ የሚመራው የጋራ ግብረሃይል ቅኝት ማድረግ መጀመሩም የቀይ ባህር ጉዞን ወደቀደመ ስፍራው እንደሚመልሰው ታምኖበታል።
ይሁን እንጂ የሃውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር በሚጓዙ የእስራኤል መርከቦች ላይ በቀን ሁለት ጊዜ ጥቃት እናደርሳለን የሚል ማስጠንቀቂያቸውን በዛሬው እለት አውጥተዋል።
የስዊዝ ቦይ፤ የስድስት ቀናቱ ጦርነት፤ የዮም ኪፑር ጦርነት
ግብጽ የአለማችን በጣም ስራ የሚበዛበት ቦይ በፈረንጆቹ 1956 የመንግስት ንብረት አድርጋዋለች።
ይህም በስዊዝ ቦይ የባለቤትነት ድርሻ የነበራቸው ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ከእስራኤል ጋር በመሆን ጦርነት እንዲያውጁባት ምክንያት ሆኖ ነበር። “የስዊዝ ቀውስ” የሚል መጠሪያ የነበረው ውጥረት እስራኤል 40 መርከቦችን አስጥማና አሜሪካ፣ ሶቪየት ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጣልቃገብተው መቋጫ እንዳገኘ አይዘነጋም።
ግብጽና የተወሰኑ የአረብ ሀገራት በ1967 እስራኤል ጋር ሲዋጉ (የስድስት ቀናቱ ጦርነት) የእስራኤል ወታደሮች ምስራቃዊ የስዊዝ ቦይን ለመቆጣጠር ተቃርበው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የስዊዝ ቦይ እስከ 1973 ዝግ ሆኖ ቆይቷል።
ግብጽ የስዊዝ ቦይን ሙሉ በሙሉ ዳግም የተቆጣጠረችው ከ1973ቱ የዮም ኪፑር ጦርነት በኋላ ነው። 4ኛው የእስራኤልና አረብ ሀገራት ጦርነት ወይንም የጥቅምቱ ጦርነት የሚል ስያሜ ተሰጥቶት የነበረው ጦርነት ግብጽና እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ሲደርሱ መጠናቀቁ አይዘነጋም።
ግብጽ ከእስራኤል ጋር ባደረገቻቸው ጦርነቶች ሁሉ ኢላማ የሆነውን የስዊዝ ቦይ ዳግም የከፈተችው በሰኔ ወር 1975 ነበር።
የአለማችን ዋነኛ የንግድ መርከቦች መተላለፊያ ከወደ የመን በሚተኮሱ ሚሳኤሎች የሚረበሽ ከሆነም ካይሮ ጦርነት ማዋጇ የሚቀር አይመስልም።
ተንታኞች ግን ከሳኡዲ መራሹ ጦር ጋር በመሆን የሃውቲ ታጣቂዎችን ለመዋጋት ወደ ሰንአ የዘለቀችው ግብጽ ለቡድኑ ድጋፍ ስታደርግ እንደነበር በመጥቀስ ጦርነት ከማወጅ ይልቅ ማግባባቱን ልትመርጥ እንደምትችል ያምናሉ።