የእስራኤል ጦር እንደገለጸው ባለፈው ቀን የጸረ-ታንክ ሚሳይሎችን እና የሮኬት ማስወንጨፊያ ማማዎችን ጨምሮ 300 ኢላማዎችን መትቷል
እስራኤል በጋዛ በሚገኙት ውስብስብ የመሬት ውስጥ ዋሻዎች የሀማስ ታጣቂዎች እያጠቃች መሆኗን አስታውቃለች።
ሀገሪቱ ይህን ያለችው ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ጥሪውን ውድቅ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።
ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ባልተጠበቀ ሁኔታ ድንበሯን ጥሶ ዜጎቿን የገደለባትን ሀማስን ለማጥፋት የወጠነችው እስራኤል በጋዛ መሽጎባቸዋል የተባሉት የመሬት ውስጥ ዋሻዎች ዋነኛ የጥቃት ኢላማዎቿ ናቸው።
የእስራኤል ጦር እንደገለጸው ባለፈው ቀን የጸረ-ታንክ ሚሳይሎችን እና የሮኬት ማስወንጨፊያ ማማዎችን ጨምሮ 300 ኢላማዎችን መትቷል።
ጦሩ ሀማስ በጸረ-ታንክ እና በመትረጌስ ምላሽ መስጠቱን ገለጿል።
በጋዛ ሰርጥ ይዞታውን እያስፋፋ መሆኑን የገለጸው ጦሩ "ሽብርተኞች" እና "የሽብርተኞች መገልገያ" የሆኑ መሰረተ ልማቶች እንዲወድሙ ተደርጓል ብሏል።
የአረብ ሀገራት እና አሜሪካ፣ በጋዛ ያለው የሰብአዊ ቀውስ ሁኔታ እንዳይባባስ እስራኤል በእግረኛ ጦር የምታደርጠውን ዘመቻ እንድታቆም ጠይቀዋታል።
ነገርግን እስራኤል ማጥቃቷን እንደማታቆም አሳውቃለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁም እስራኤል እየወሰደችው ያለው እርምጃ ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ መድረሱን እና ታጋቾችን ለማስለቀቅ እድሉ የሰፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።
አሜሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ቁጥር አንድ ለሆነችው አጋሯ እስራኤል ሁለት የጦር መርከቦችን በመላክ አለሁልሽ ብላታለች።
በሌላ በኩል ኢራን እና በእስሬኤል ዙሪያ ያሉ ታጣቂ ቡድኖች ለሀማስ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
ግጭቱ እንዲረግብ የተደረገው አለምአቀፍ ጥሪ እስካሁን ውጤት አላመጣም።