የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ተደራዳሪዎች ፊት ለፊት አለመገናኘታቸው ተነገረ
የሁለቱ ሀገራት ተወካዮች በተለያየ ክፍል ውስጥ በቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሸማጋይነት እየተደራደሩ ነው ተብሏል
ከሶማሊላንድ ጋር በተፈረመው የወደብ የመግባብያ ስምምነት ዙርያ ሀገራቱ በቱርክ ሁለተኛ ዙር ንግገራቸውን ትላንት ጀምረዋል
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ እያደረጉት የሚገኝው ድርድር ቀጥተኛ ባለሆነ መንግድ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተነገረ፡፡
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የወደብ የመግባባያ ስምምነት ተከትሎ በዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ላይ የሚገኙት አዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ በቱርክ እያደረጉ የሚገኙትን ሁለተኛ ዙር ድርድርድ በትላንትናው እለት ጀምረዋል፡፡
በቱርክ አንካራ የሚገኙት የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በተለያየ ክፍል ተቀምጠው የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሃካን ፊዳን ከሁለቱ ልዑካን ጋር ለየብቻ በመገናኘት ድርድሩን እየመሩ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
ቪኦኤ ድርድሩን እያስተባበሩ ከሚገኙ የውስጥ ምንጮች አገኝሁት ብሎ እንደዘገበው ሃካን ፊዳን በትላንትናው እለት ከሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ጋር ሁለት ጊዜ ለየብቻ ተገናኝተዋል፡፡
ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው የመግባብያ ስምምነት እጣፈንታ የሀገራቱ የድርድር ውጤት እንደሚወስን የድርድር አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡
አክለውም የመግባብያ ስምምነቱ እና ኢትዮጵያ የወደብ አቅርቦት በምታገኝበት ሁኔታ ሀገራቱ ያላቸውን ልዩነት ለማጥበብ ጠንካራ ድርድር እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡
ድርድሩ ትላንት ከመጀመሩ በፊት የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶሀን ከሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ሀገራቱ ወደ እርቅ እና ሰላም እንዲመለሱ ጠይቀዋል፡፡
ኤርዶሀን ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀመድ ጋር ያደረጉትን የስልክ ቆይታ አስመልክቶ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ በሁለተኛው ዙር ድርድር ወሳኝ የመግባብያ ነጥብ ላይ በሚደረስበት ሁኔታ ላይ መመክራቸውን አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያ የሶማሊያን ግዛታዊ አንድነት እና ሉአላዊነት ስጋት ውስጥ ከሚከቱ ሁኔታዎች እንድታስወግድ ጥሪ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህን ተከትሎ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በተመሳሳይ በኤክስ ገጻቸው ላይ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር የኢኮኖሚ እና ልማት ትብብሮችን ለማስቀጠል ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡
ከወራት በፊት ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ በተፈራረሙት የመግባብያ ስምምነት ኢትዮጵያ በኤደን ባህረ ሰላጤ ለ50 አመታት በሊዝ ኪራይ የሚቆይ 20 ኪሎሜትሮች የሚረዝም የባህር ጠረፍ እንድታገኝ እና በምላሹ አዲስ አበባ ለሶማሊላንድ እውቅና እንድትሰጥ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀው ነበር፡፡
ይህን ተከትሎም በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት መፈጠሩ አይዘነጋም።